ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በንግዱ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በንግዱ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)።
በአፋር ክልል የተገነባው የሰመራ ሁለተኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ እና ሚኒስትሩ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ ካደረገች ወዲህ ከቁም እንስሳት ዘርፍ የምታገኘው ገቢ ጨምሯል።
ለአብነትም ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከዘርፉ 39 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ዛሬ የተመረቀው ማዕከል ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባ ሲሆን፥ በተለያዩ አካባቢዎች ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 10 ማዕከላት እየተገነቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ1ሺህ 950 በላይ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በመላ ሀገሪቱ እንደሚገኙ ገልጸው፥ እነዚህን ገበያዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ በበኩላቸው፥ የማዕከሉ ወደ ስራ መግባት በክልሉ የሚገኘውን ሰፊ የእንስሳት ሀብት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ጥቅም መለወጥ ያስችላል ብለዋል።
ማዕከሉ ለሚሌ የእንስሳት ማቆያ ቅርበት ያለው በመሆኑ የእንስሳት ወጪ ንግድን ለማሳለጥና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡