Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያዊያንን ያስቀደመው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ …

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ ዓመታት ዜጎችን ያስቀደመው ‘ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ’ አያሌ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡
ከለውጡ በፊት በውጪ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ይክፋቸውም ይልማቸው ጆሮ እና ዐይን የሌለው ጉዳያቸው ጉዳዩ ያልሆነ መንግስት እንደነበራቸው በርካታ ማጣቀሻዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡
ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ተለያዩ ሀገራት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ባመሩባቸው የተለያዩ ሀገራት የኢትዮጵያውያን የኑሮ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን መፈተሻቸውን ማንሳት ይቻላል።
ባሉበት ሀገር የተሳካ ህይወት የሚመሩትን በማበረታታት እንዲሁም ደግሞ ችግር የገጠማቸው መፍትሄ ያገኙ ዘንድ እገዛ ያደርጋሉ።
እስር ቤት መግባትን ጨምሮ የከፋ የህይወት መስመር ውስጥ የሚገኙትን ደግሞ ለሀገራቸው እንዲበቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጓዙበት አውሮፕላን ይዘው በመመለስ መንግሥት ለዜጋ ያለውን ከፍተኛ ክብር በተግባር አሳይተዋል።
የለውጡ መንግሥት ዜጎች ወደ ውጪ ሀገራት ሄደው እንዲሰሩ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ከሀገራቱ መንግሥታት ጋር ህጋዊ ስምምነት በመፈጸም የስጋት ተጋላጭነታቸውን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በዚህም ዜጎች መብታቸው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን መርዳት እዲችሉ እየተደረገ ነው።
ባለፉት ዓመታት በመካከለኛው ምስራቅ በችግር ውስጥ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ሀገር እንዲገቡ ለማድረግ በርካታ ተቋማት የተቀናጀ እና የተናበበ ስራ ሰርተዋል።
በተለይም ከሚያዚያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሶስት ወራት በሳዑዲ ዓረቢያ በተለያየ ማቆያ ጣቢያ የሚገኙ 70 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገር እንዲመለሱ የተደረገው ጥረት እና የተመዘገበው ውጤት በምሳሌነት ይጠቀሳል።
በዚህም ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ህይወታቸው መስመር እንዲይዝ የሚያስችል ድጋፍና ክትትል ተደርጎላቸዋል፤ እየተደረገላቸውም ይገኛል።
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.