Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲጂታል የሰነድ ማረጋገጥ አገልግሎት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰነድ ማረጋገጥ አገልግሎትን በዲጂታል መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ቴሌሳይን የተሰኘ አሰራር ይፋ ተደርጓል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ጉዳይ እና ከፍትህ ሚኒስቴር እንዲሁም ከፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን፥ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ድንበር ተሻጋሪና ዜጋ ተኮር አገልግሎቶችን ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሚኒስቴሩ ያስጀመረው ዲጂታል አሰራር ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡

ተቋማዊ ዲጂታላይዜሽንን ዕውን የሚያደርግ ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነ አገልግሎት መሆኑን ገልጸው፥ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባባበር የቴሌ ፊርማ (tele sign) የተሰኘ አገልግሎት ይፋ መደረጉን ተናግረዋል።

የሰነድ ማረጋገጥ አገልግሎቱ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ፣ ዲጂታል ፊርማ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ የቪዲዮ ማረጋገጫን የሚጠቀም ሲሆን፥ ማህበራዊና ኢኪኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

ሚኒስቴሩ የሰነድ ማረጋገጥ አገልግሎትን በዚሁ ዲጂታል አሰራር አማካኝነት በኦንላይን ብቻ ማስተናገድ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው፥ የቴሌ ዲጂታል ፊርማ በአገልግሎት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ዜጎችና ተቋማትን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በርካታ ተቋማትን ያስተሳሰረው አገልግሎቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ እንዲሁም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀሚድ ከኒሶን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.