Fana: At a Speed of Life!

ታዳጊዋን አግተው ከወላጇ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የወሰዱ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት አንድን ታዳጊ አግተው ከወላጅ አባቷ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የወሰዱ በ18 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ወሰነ።

የቅጣት ውሳኔ የተወሰነባቸው ተከሳሾች ብሬ በላይ፣ ፍሮምሳ በላይ እና ያደቴ ተፈራ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

የሸገር ከተማ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 670 ንዑስ ቁጥር 1 እንዲሁም የጦር መሳሪያ ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸው በመጥቀስ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በክሱ ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሾች ገንዘብ አዋጥተው በህገ ወጥ መንገድ አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ በመግዛትና የፀጥታ አካላት አልባሳትን በመልበስ በተጨማሪነት 3ኛ ተከሳሽ የወላጅ አባቱን ክላሽንኮቭ መሳሪያ ደብቆ አውጥቶ በመያዝ በጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ከምሽቱ 7 ሰዓት ሲሆን በሸገር ከተማ ገላን እንዶዴ አካባቢ የግለሰብ ቤት አንኳክተው በመግባትና በጦር መሳሪያ በማስፈራራት ብሩኬ አበራ የተባለች ታዳጊን አግተው በሰበታ ከተማ አዋስ ወረዳ ጫካ ውስጥ ለ3 ቀን በመሸሸግ ወላጅ አባቷ ጋር ስልክ በመደወል 5 ሚሊየን ብር እንዲከፍል ጠይቀዋል።

ገንዘቡ የማይከፈል ከሆነ በታጋቿ ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ ሲያስፈራሩ ቆይተው የታጋች ወላጅ አባት ያለው ገንዘብ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን መሆኑን ገልጾ ገንዘቡን እንደከፈላቸው በክሱ ላይ ተመላክቷል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሾቹ ታጋቿን ይዘው የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ውስጥ ብስኩት ሲገዙ የተመለከቱ ግለሰቦች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መነሻ በተደረገ ክትትል በዕለቱ አጋቾቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸው በክሱ ላይ በዝርዝር ሰፍሯል።

ተከሳሾቹ ከግል ተበዳይ ወላጅ አባት አስፈራርተው ከተቀበሉት ገንዘብ ውስጥ 785 ሺህ 900 ብር በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሽ ወላጅ አባት እርሻ መሬት ውስጥ ከጦር መሳሪያው ጋር ቀብረው የተገኘ ሲሆን ቀሪ ብሩን ማጥፋታቸው መረጋገጡም ተጠቅሷል።

ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር ፍርድ ቤት ቀርበው የደረሳቸው ሲሆን፤ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች እገታውን መፈጸማቸውን ቢያምኑም ገንዘብ መቀበላቸውን በሚመለከት ክደው ተከራክረዋል።

በዚህም በተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ተከሳሾች በተከሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ ብይን ሲሰጥም፤ ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮና ይዞ ተከሳሾችንና ሌላውንም ያስተምራል በማለት ወንድማማች የሆኑትን 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾችን በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

3ኛ ተከሳሽን በተመለከተ እድሜው 17 ዓመት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በ17 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፏል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.