Fana: At a Speed of Life!

በላብ የሚጸና ሉዓላዊነት…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት ግዛታዊ አንድነቷን የተዳፈሩ ኃይሎችን በጀግንነት መክታ በልጆቿ ደም ሉዓላዊነቷን አስከብራ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡

ግዛታዊ አንድነቷ ተከብሮና ጎተራዋን ሞልታ ሉዓላዊት እና የልማት ቀንዲል ሆና እንድትቀጥል ደግሞ ከደም መስዋዕትነት ባሻገር የዜጎቿን ወዝ ትፈልጋለች፡፡

የለውጡ መንግስት በ2011 ዓ.ም ያስጀመረው የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት ኢትዮጵያ ከተመጽዋችነት ራስን ወደመቻል በምታደርገው ጉዞ የታሪክ እጥፋት መሆን ችሏል፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት የአጋጣሚ ሳይሆን ሂደቱንና ግልጽ መዳረሻውን አስቀድሞ በተለመ ስትራቴጂና ውጤታማ ትግበራ የተገኘ ነው፡፡

የመስኖ ልማትን በማስፋት፣ የተሻሉ ዝርያዎችን በማቅረብ፣ ዘመናዊ አስተራረስን በማጠናከርና አርሶ አደሮችን በማቀናጀት ረገድ የተሰሩ ስራዎች በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እንዲመዘገብ አስችለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ አሃዛዊ መረጃዎች በምግብ ራስን የመቻል ርዕይን በሰነቀው ሀገራዊ የስንዴ ልማት ለተገኘው ውጤት ሁነኛ አስረጂ ናቸው፡፡

በ2011 ዓ.ም በ3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ በተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በወቅቱ 100 ሺህ ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሎ ነበር፡፡

ባለፉት ዓመታት በእርሻ ሽፋን እንዲሁም በምርትና ምርታማነት ከፍተኛ እድገት የተመዘገበ ሲሆን÷ በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 29 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዷል፡፡

በዘንድሮው ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ174 ነጥብ 99 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡

በየዓመቱ እስከ 1 ቢሊየን ዶላር በማውጣት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ባሻገር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከቁጥር ባለፈ የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት በመቀየርና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ለአፍሪካ አብነት የሚሆን ስኬት እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.