Fana: At a Speed of Life!

እያደገ የመጣው የኮንፈረንስ ቱሪዝም

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እያደገ የመጣው የኮንፈረንስ ቱሪዝም ኢትዮጵያን በአፍሪካ የዲፕሎማሲና የንግድ መድረክ ቀዳሚ ተመራጭ እያደረጋት ይገኛል።

መንግሥት ያከናወናቸውን መጠነ-ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተከትሎ በዘርፉ መነቃቃት በመፍጠር በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖዎች አሳርፏል።

በዚህም የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መድረክ ተመራጭ መዳረሻ ሆናለች።

ለዚህም አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የወዳጅነት ፓርክ እና የሳይንስ ሙዚየም ያሉ ዘመናዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ለዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መዲናዋ ያላትን ዝግጁነትና ውበት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ ቁልፍ ስራዎች ናቸው።

ዓለም አቀፉ የኮንግረስ እና የኮንፈረንስ ማኅበርም አዲስ አበባ ከፍተኛ ታዳሚ የመያዝ አቅም ያላቸውን የመሰብሰቢያ ማዕከላትን በማልማት በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በብቃት እያስተናገደች እንደምትኝ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ይህ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ለውጥ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን ወደ ክልል ከተሞችም በስፋት በመሸጋገር እንደ አዳማ፣ ባህር ዳር፣ አርባ ምንጭ፣ ድሬዳዋ፣ ጅማ እና ሀዋሳ ያሉ ከተሞች በዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሾችና በከፍተኛ ደረጃ እያደገ በመጣው የሆቴል ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ መሆን የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የሆቴሎች ቁጥር መበራከትም የክልል ከተሞች ብሔራዊና ቀጣናዊ ስብሰባዎችን በብቃት እንዲያስተናግዱ ዕድል በመፍጠር፣ የቱሪስት ፍሰቱ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሰራጭና የአካባቢው ማኅበረሰብን ተጠቃሚነት አረጋግጧል።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገቱ በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያመጣው ውጤት እጅግ አበረታች መሆኑን ቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል።

የዘርፉ ማደግ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው አስተዋጽኦ በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ በዘርፉ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።

ይህ ስኬት ወደፊትም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ግንባር ቀደም የቢዝነስና የጉባኤ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ እንደ ዋና ሞተር ሆኖ ያገለግላል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.