Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ በአዲስ አበባ መጀመሩ ትክክለኛ ውሳኔ ነው – ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ በአዲስ አበባ መጀመሩ ትክክለኛ ውሳኔ ነው አሉ ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም።

ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም ቀደም ሲል የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ በመሆን ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ እና ተሣታፊዎችን የመለየት ስራ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው የምክክር መድረክ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ከትግራይ እና ከአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ታዳሚያን እየተሳተፉበት ነው።

ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም እንደገለጹት÷ ዋናው የሀገራዊ ምክክር መድረክ ዓላማ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ዓይነት ጥያቄዎች እና ችግሮች በጦርነትና በጉልበት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፈታት አለባቸው የሚል ነው።

ከሚሽኑ የውይይት መድረኩን በትግራይ ክልል ለማካሄድ በተለያዩ ጊዜያት ብርቱ ጥረት ቢያደርግም በክልሉ ያለው በኃይል ብቻ የሚተማመነው እና ለሰላማዊ ውይይቱ ፈቃደኛ ያልሆነው ህገ-ወጥ ቡድን አማካኝነት ለማካሄድ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ትግራይ ከሌሎች ክልሎች የተለየች አይደለችም ያሉት ወይዘሮ ኬርያ÷ በትግራይ ክልል ምቹ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ የውይይት መድረክና አጀንዳ የማሰባሰብ ስራው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መደረጉ ትክክለኛና አግባብነት ያለው ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።

ዋናውን የኮሚሽኑን ተልዕኮ ለማሳካት ወደ ውይይት መድረክ መምጣትና ችግሮችን በመመካከር መፍታት አዋጭነት ያለው መሆኑንም አስረድተዋል።

በሰላም እና በውይይት የሚያምን የትግራይ ማህበረሰብ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው የምክከር መድረክና አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ላይ በቀናነት እየተሳተፈ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተለያዩ ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አንስተው÷ የትግራይ ክልል ጥያቄዎችና ችግሮች በመመካከር በመወያየት እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚፈቱ እንደሆኑ አፅንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.