Fana: At a Speed of Life!

የተረሳው የብራዚል ወርቃማው ልጅ አድሪያኖ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእግር ኳስ ችሎታው ዓለምን ያነጋገረ ድንቅ ጥበበኛ ነበር የብራዚል ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች አድሪያኖ፡፡

አድሪያኖ እግር ኳስን የጀመረው በሀገሩ ክለብ ፍላሚንጎ ሲሆን በፈረንጆቹ 2002 የጣሊያኑን ክለብ ኢንተር ሚላን ተቀላቅሏል።

ለኢንተር ሚላን 8 ጨዋታዎችን ካደረገ በኋላ ለሁለት የውድድር ዓመት ለፓርማ እና ፊዮሬንቲና በውሰት ውል ተጫውቶ አሳልፏል፡፡

ከሁለት የውድድር ዘመን የውሰት ቆይታ በኋላ በድጋሚ ወደ ኢንተር ሚላን በመመለስ ምርጥ ብቃቱን ማሳየቱ ይታወሳል፡፡

በኢንተር ሚላን በምርጥ እንቅስቃሴው የቀጠለው አድሪያኖ ለጣሊያን ሴሪ አ ተከላካዮች እጅግ ፈታኝ የፊት መስመር ተጫዋች ነበር፡፡

ለጣሊያኑ ክለብ ኢንተር ሚላን 177 ጨዋታዎችን አድርጎ 74 ግቦችን ያስቆጠረው አድሪያኖ የጣሊያን ሴሪ አ፣ ኮፓ ኢታሊያ እና የሱፐር ኮፓ ዋንጫዎችን ከቡድኑ ጋር አሳክቷል፡፡

የብራዚል ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ኮከብ አድሪያኖ ወደ ግብ በሚመታቸው ጠንካራ ኳሶች ይታወቅ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን ያሸነፈ ሲሆን፥ በብዙዎች ዘንድ የሮናልዶ ሊዊስ ናዛሪዮ ዴሊማ ትክክለኛ ተተኪ ተብሎ ተቆጥሮ ነበር፡፡

በፈረንጆቹ 2016 እግር ኳስን ያቆመው አድሪያኖ ለሀገሩ ብራዚል 48 ጨዋታዎችን አድርጎ 27 ግቦችን አስቆጥሯል።

የፈረንጆቹ 2004 የብራዚላዊው ኮከብ አድሪያኖ የእግር ኳስ ሕይወት መበላሸት የጀመረበት ጊዜ ነበር።

በወቅቱ ከብራዚል ስልክ ተደውሎ አባቱ ማረፉ የተነገረው አድሪያኖ አባቱን በሞት ካጣ በኋላ በቀደመ የእግር ኳስ ችሎታው መቀጠል አልቻለም፡፡

ከዚያ ጊዜ በኋላ ሃዘኑን ለመርሳት የአልኮል መጠጥ ቤቶችን ያዘወተረው አድሪያኖ እየጠጣ በየጎዳናው ወድቆ ይታይ ነበር፡፡

ወላጅ አባቱ ከሌላቸው ላይ ለእግር ኳስ አካዳሚዎች እየከፈሉ የአድሪያኖን ሕይወት ለማሳመር ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡

በወቅቱ የ22 ዓመት ወጣት የነበረው አድሪያኖ አባቱን ካጣ በኋላ ጭንቀቱን ለመርሳት መጠጥ ቤት ያዘወትር ነበር፡፡

የኢንተርሚላን ተጫዋች በነበረበት ጊዜ ወደ ልምምድ ሜዳ ሲመጣ መጠጥ ጠጥቶ እስከመምጣት ደርሶም ነበር፡፡

የኢንተር ሚላን ኃላፊዎች አድሪያኖን ለማገዝ ቢሞክሩም እሱ ግን ሊሰማቸው ፍቃደኛ ባለመሆኑ ከክለቡ ጋር ለመለያየት ተገድዷል፡፡

ከኢንተር ሚላን ጋር ከተለያየ በኋላ ሮማ፣ ሳኦፖሎ፣ ፍላሚንጎ፣ ኮረንቲያስ፣ አትሌቲኮ ፓራኔንሴ እና ማያሚ ዩናይትድ የመሳሰሉ ክለቦችን ቢቀላቀልም የቀድሞ አድሪያኖ ግን ሜዳ ላይ አልነበረም፡፡

ከዚያ በኋላ መኖሪያውን በሀገሩ ብራዚል ያደረገው አድሪያኖ በተለያየ ጊዜ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል፡፡

በ2021 ቅንጡ አፓርታማ መኖሪያ ቤቱን እንደሸጠ የሚነገረው አድሪያኖ ብዙ ጊዜ ጎዳና ላይ በባዶ እግሩ ሲንቀሳቀስ ይታይ ነበር፡፡

የ44 ዓመቱ አድሪያኖ አሁን ከዚያ አስቸጋሪ ሕይወት በመውጣትና ለሰላሙ ቅድሚያ በመስጠት መደበኛ ሕይወቱን በሀገሩ ብራዚል እየኖረ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.