በለውጡ ዓመታት የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የዲጂታል እድገት አስመዝግቧል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ መንግሥት ቴሌኮሙኒኬሽን ለግል ዘርፉ ክፍት በመሆኑ በአፍሪካ ፈጣን ከሚባሉ የዲጂታል ዕድገቶች አንዱን አስመዝግቧል አለ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት።
ጽ/ቤቱ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ወደ ዘመናዊና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚ በሚል ያለፉትን ስምንት የለውጥ ዓመታቱ ጉዞ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የፋይናንስ ተደራሽነትን ስኬቶች አብራርቷል።
በዚህም ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የሞባይል ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ37 ነጥብ 9 ሚሊየን ወደ 87 ነጥብ 9 ሚሊየን በማደግ ተደራሽነትና አካታችነትን ማስፋቱን ገልጿል።
የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎትም ከ58 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎችን ማፍራቱን አንስቷል።
የገንዘብ ዝውውሩ ከ7 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር በላይ በመሻገር የፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነት እውን እንዲሆን ማስቻሉን ጠቅሷል።
የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎች ማክሮ ኢኮኖሚን እያረጋጉ እንደሆነ ገልጾ፤ የባንኮች ብድር ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ሁኔታ ለመንግሥትና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደነበረ አስታውሷል።
ከኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተናበበ ሁኔታ የግል ዘርፉ የባንኮች ብድር ድርሻ ከፍተኛ እንዲሆን በመደረጉ የግሉ ዘርፍ ከአጠቃላይ በባንኮች የሚሰጠው ብድር የሚያገኘው ድርሻ ከ85 በመቶ በላይ ሆኗል ነው ያለው።
በለውጡ የመንግሥት ባንኮችን መልሶ ማዋቀርና የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት በማስጠበቅ የገንዘብ ፍሰትን ማሻሻል የተቻለ ሲሆን የሀብት ጥራትን በመጨመር የፋይናንስ ዘላቂነትን ማጎልበት መቻሉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በመረጃው አመልክቷል።