የአማራ ክልል ለ1 ሺህ 224 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የክልሉ መስተዳድር ም/ቤት በወሰነው መሰረት ለ1 ሺህ 224 ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል፡፡
የቢሮው ም/ሃላፊ አያሌው አባተ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ መስተዳድር ም/ቤቱ ባካሄደው 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባዔ ለታራሚዎች ይቅርታ እንዲደረግ ወስኗል፡፡
ውሳኔው የታራሚዎች ይቅርታ አወሳሰን መመሪያ እርቅ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ባመነባቸው ጉዳዮች እርቅ የፈጸሙና እና ለተበዳዮቹም ካሣ የከፈሉ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተላለፈ ነው ብለዋል፡፡
በሴቶችና ሕጻናት ላይ ወንጀል የፈጸሙና በከባድ ወንጀሎች በመሳተፍ የዕድሜ ልክ እሥራት የተወሰነባቸው ታራሚዎች የይቅርታው አካል አይደሉም ነው ያሉት፡፡
ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ያገኙትን ሥነ ምግባር፣ ክህሎትና ታማኝነት በማሕበረሰቡ ውስጥ በማሳየት አምራችና ሕግ አክባሪ ዜጋ መሆን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ