የአዲስ ስፖርት ፓርክ የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ ልማት የሚያሳይ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ ስፖርት ፓርክ የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ ልማት የሚያሳይ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ የኢኮኖሚ ልማት ያለ ሰብአዊ ልማት ምልዑ ሊሆን አይችልም፤ የስፖርት መሰረተ ልማት ማስፋፊያዎቻችንም የዚሁ ተግባር ማሳያዎቻችን ናቸው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት እሳቤ ሁሉን አቀፍ ልማት ለዜጎቹ ተደራሽ ማድረግ ነው ሲሉም አመላክተዋል።
ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ የተከፈተው እና በፈጣን አፈጻጸም ተገንብቶ የተጠናቀቀው የአዲስ ስፖርት ፓርክ የመደመር መንግሥት እሳቤ እና ተግባር የተገናኙበት የስፖርት አውድ ነው ብለዋል።
ፓርኩ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የሁሉም ስፖርቶች መሠረተ ልማት እና የአረንጓዴ መዝናኛ ስፍራን ባሟላ መልኩ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፓርኩ ለወጣቶቻቾን መወዳደሪያና ለታዳጊዎቻችን መጎልበቻ ከመሆን ባለፈ የስፖርት ፈርጦቻችን ሐውልት የቆመበት የጀግኖቻችን አምባ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
በስፖርት ፓርኩ የጀግኖቻችን ገጽ ከነጽናታቸው፤ ከነብርታታቸው፣ ከነአርዓያነታቸው ፊታቸው ላይ ከተጻፈው የሀገር ፍቅር ጋር ተደምሮ ሐውልት ሆኖ ቆሟል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እነዚህ ሐውልቶች ለኢትዮጵያ የሮጡ እግሮች፣ ለሀገር ከተከፈለ ውድ ዋጋ እና ክብራቸው ጋር ተቀርጾ በክብር ተሰይሟል ብለዋል።
የመደመር መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል አስምሮ፤ መንግሥት የመሆንን ኃላፊነት አክብሮ እየሰራ ስለመሆኑ ከሚመሰክሩ ተግባራት መካከል ዛሬ ተመርቆ ክፍት የሆነው የአዲስ ስፖርት ፓርክ ማሳያ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
ቃል ተግባር እየሆነ አዲስ አበባም እየተቀየረች፣ ኢትዮጵያም እየለማች፤ ወደ ክብር ማማ እየገሰገሰች ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።