Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በጸረ ሽብር ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በጸረ ሽብር ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡

በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከኢሚሬቶች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የጽንፈኝነትና የሽብርተኝነት መከላከል ልዩ መልዕክተኛ ማቅሱድ ክሩዝ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር)÷ በዚህ ፈታኝ ወቅት ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ጋር ያላትን ሙሉ አጋርነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በጸረ ሽብር ተግባራት ላይ ስላላት ንቁ ተሳትፎና ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ስለሚገኘው አስተዋጽኦ ለልዩ መልዕክተኛው ገለጻ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በጸረ ሽብር ዘመቻዎች፣ በድንበር ደህንነትና በቀጣናዊ የሰላም ጥረቶች ላይ ባላት ተሳትፎ በአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የደህንነት ዋልታ ሆና ማገልገሏን እንደምትቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል።

ማቅሱድ ክሩዝ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኤሚሬቶች ስትራቴጂካዊ አጋሮች መሆናቸውን ገልጸው ÷ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሀገሪቱ ያደረጉት ጉብኝት የማይረሳና ታሪካዊ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ኤሚሬቶች ጽንፈኝነትንና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን አጠቃላይ ጥረት እንዲሁም የቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ቅንጅት ሥራዎች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በጸረ ሽብርተኝነትና በጽንፈኝነት መከላከል ረገድ ያላቸውን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸውንም ኤምባሲው ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.