Fana: At a Speed of Life!

አደገኛ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ይትባረክ ዳዊት ከነግብረአበሮቹ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረ አደገኛ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ይትባረክ ዳዊት (ክብሮም)ን ከነግብረአበሮቹ በቁጥጥር ስር አውሏል።

ከ3 ሺህ በላይ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር፣ ከ100 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገ እና ከ50 በላይ ሴቶች እንዲደፈሩ ያደረገው ይትባረክ ዳዊት (ክብሮም)ን ከ9 ግብረአበሮቹ ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ አጠናቅቆ ለዓቃቢ ህግ መላኩን ነው ፌደራል ፖሊስ ያስታወቀው።

ይህንን ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ምርመራ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሚሰራ The Regional Operational Centre in support of the Khartoum process (ROCK) ከተባለ ድርጅት ጋር ባደረገው የመረጃ ልውውጥ ነው በቁጥጥር ስር ያዋለው።

በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረው አደገኛ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ይትባረክ ዳዊት አለሙን በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ላይ ፖሊስ በቅንጅት በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገልጿል።

ተጠርጣሪው በፓስፖርት ስሙ ይትባረክ ዳዊት አለሙ ቤተሰቦቹ በልጅነቱ ያወጡለት ስም ጳውሎስ ዳዊት ወልዳይ ወንጀል መስራት ሲጀምር የሚታወቅባቸው ስሞች አድሀኖም ሱዳን፣ አህመድ ሱማሊያ ጅቡቲ እና ኬንያ የሚጠቀምበት ስም ሙኒር ሲሆን ክብሮም ደግሞ በስዊድን እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የሚጠቀምባቸው ሀሰተኛ ስሞች መሆናቸውን ፖሊስ በምርመራው ማረጋገጡ ተጠቁሟል፡፡

ፖሊስ እነዚህን ስሞች ለምርመራው አጋዥ አድርጎ ያደገ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተጠናከረ ምርመራና ክትትል በማድረግ ከ70 በላይ በሀገር ውስጥና በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዋና ዋና የሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን ከለየ በኋላ ዋናውን ተጠርጣሪ ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ተከታትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ፖሊስ የተያዙትንም ሆነ ያልተያዙትን ተጠርጣሪዎች በወንጀሉ ያፈሩትን ሀብት በጥናት በመለየት ሌሎች ሀብቶቻቸውንና በባንክ የሚገኝ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ በፍርድ ቤት እንዲታገድ ማድረጉን ገልጿል፡፡

ሕገ ወጥ አዘዋዋሪ ቡድኑ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ወጣቶችን ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በመመልመል ወደ ሊቢያ በመውሰድ ሊቢያ ውስጥ ባዘጋጁት መጋዝን እንዲታገቱ ማድረጋቸው ነው የተገለጸው፡፡

ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመፈፀም በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው፣ ሴቶች እንዲደፈሩ እና ከፍተኛ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጋቸውን ፖሊስ በምርመራ ማረጋገጡ ተጠቅሷል፡፡

ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሊቢያ ውስጥ ተጎጂዎችን አግተው የሚያሰቃዩባቸው አምስት ማከማቻ መጋዘን እንዳላቸው እና በዚህ አደገኛ ወንጀል ከ3 ቢሊየን ብር በላይ በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ፖሊስ በሰበሰበው ማስረጃ ማረጋገጡ ተመላክቷል፡፡

በዚህም ከ100 በላይ ተጎጂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምስክርነት ቃል የመቀበል ሥራ መሰራቱን ገልጿል፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ቤልጂየም፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድ፣ ሉግዘንበርግ እና ስዊዘርላንድ ከሚገኙ 16 ተጎጂዎች ላይ ቃል መቀበሉንም ፖሊስ አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሀገርና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን ይህንን ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ለመከላከል ዘመኑ ያፈራቸውን የምርመራ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በተሟላ ፖሊሳዊ ስብዕናና ስነ ምግባር እየተመራ በላቀ ቁርጠኝነት ተልዕኮውን መወጣቱ ተገልጿል፡፡

ተቋሙ ከሀገራት ጋር በፈጠረው የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነት ዓለም አቀፍ የወንጀል ተፈላጊዎችን ጭምር በቁጥጥር ሥር አውሎ በተለያየ ጊዜ ምርመራ በማጣራት በሀገር ውስጥ በሕግ እንዲጠየቁና የተወሰኑት ደግሞ ከሀገራት ጋር ባለው የወንጀለኛ ልውውጥ ስምምነት መሰረት ተላልፈው እንዲሰጡ እያደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ሕብረተሰቡ ማንኛውንም የወንጀል ድርጊት ሲመለከት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፣ በ991 ነፃ የስልክ መስመር እና ሰው አልባ ፖሊስ ጣቢያ በመጠቀም ወይም በአቅራቢያው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የዘወትር ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተቋሙ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.