2ኛው የኢትዮጵያ እና ብሩንዲ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 2ኛው የኢትዮጵያ እና ብሩንዲ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
ስብሰባው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በመከላከያ እና ጸጥታ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ስምምነቶችን ለመፈጸምና አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለመለየት ያለመ ነው፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ መድረኩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ነው፡፡
በአቪዬሽን፣ በግብርና፣ በመሰረተ ልማት፣ በኃይል እና ኢንዱስትሪ ዘርፎችን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
የቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለትዮሽ ግንኙነት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ኤጊድ ንዲኩሪዮ በበኩላቸው፥ ይህ ስብሰባ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ለማላቅ ይበጃል ነው ያሉት፡፡
በስብሰባው ላይ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽኑ በሁለቱ ሀገራት የተወከሉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ባቀረቧቸው ልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡