የሀገራዊ ምክክር ሂደትን ተመካካሪው ህዝብ ከሚኖርበት አካባቢ ውጪ የማካሄድ አንድምታ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራችን ኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል በሃሳብ ልዮነቶች ለተፈጠሩ አለመግባባቶች በምክክር መፍትሔን ለማፈላለግ እየሰራ የሚገኝ የዲሞክራሲ ተቋም ነው፡፡
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ጉዞው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት አጀንዳን በሕዝባዊ ውይይቶች ማሰባሰብ ችሏል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንትም ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላትና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳን በአዲስ አበባ ከተማ ማሰባሰቡ ይታወቃል፡፡
እንደሚታወቀው በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በተደረጉ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከተመካካሪው ሕብረተሰብ አካባቢ ውጪ የምክክር ሂደቶችን ማከናወን የተለመደ አሰራር ነው፡፡ የኮሎምቢያ የዕርቅና የሀገራዊ ምክክር ሂደት ለዚህ ዐብይ ምሳሌ መሆን የሚችል ሲሆን በኩባ (ሀቫና) የተካሄደው ሂደት ተጠቃሽ ነው፡፡
የትግራይ ክልል የምክክር ሂደትን ከክልሉ ውጪ መደረጉ የተለያዩ ዓላማዎች እና መነሻዎች የነበሩት ሲሆን የሚከተሉት ሃሳቦችም ይህንን ያብራራሉ፡፡
1. የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ከማስቀጠል አንፃር
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለማከናወን ምቹ ጊዜ ሲጠባበቅ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ ከተሰጠው የጊዜ ገደብ እና የሥራ ኃላፊነት አንፃር አማራጭ መንገዶችን በመቀየስ የምክክር ሂደቱን ማስቀጠል ነበረበት፡፡ በሂደቱም ዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ከመተግበራቸው በላይ በክልሉ ባለድርሻ አካላት መካከል የመተባበር እና የተሻለ ግንኙነት እንደደረጀ ኮሚሽኑ ያምናል፡፡
ከዚህ አኳያ የክልሉ ባለድርሻ አካላት በሂደቱ ላይ ያላቸው የባለቤትነት እንደጨመረ ይታመናል፡፡ በተጨማሪም ይህ ሂደት ዜጎች የመመካከርን አስፈላጊነት የበለጠ እንዲገነዘቡና ፍላጎት እንዲያድርባቸው በር የከፈተ እንደነበር ኮሚሽኑ ያምናል፡፡
2. የዜጎችን የደህንነት ስጋቶች ከመቀነስ አንፃር
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚያካሂዳቸው የምክክር ሂደቶች ለተሰብሳቢዎች ደህንነት ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ሂደቱ ነፃነትን እና ነፃ ሃሳብ የሚሻ እንደመሆኑ ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩ ባሻገር በሂደቱ ተሳትፎ ያደረጉ ባለድርሻ አካላት በነቃ እና በባለቤትነት መንፈስ ሃሳባቸውን ያንሸራሸሩበት እና ትላልቅ ጉዳዮችን የጋራ ለማድረግ የቻሉበት መልካም አጋጣሚን እንደፈጠረ መረዳት ይቻላል፡፡
3. የሂደቱን ዲሞክራሲያዊነት ሌሎች እንዲረዱት ከማስቻል አንፃር
ለሶስት ቀናት በተደረገው የክልሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ዜጎች ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ገንቢ የሆኑ ውይይቶችን በማድረግ ራሳቸው በወከሏቸው ወኪሎች አማካኝነት የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ለመሳተፍ ከትግራይ እና ከአዲስ አበባ ጥሪ የቀረበላቸው አካላት ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ቁልፍ ጉዳዮች በአጀንዳ መልክ ማቅረባቸው በሂደቱ በተለያየ አጋጣሚ ሳይሳተፉ ለቀሩ እና ከሂደቱ ራሳቸውን ያቀቡ አካላት ስለ ሂደቱ የሚኖራቸውን ዕይታ እና ግንዛቤ እንዲሻሻል መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ኮሚሽኑ ያምናል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን