በሁሉም ውደድሮች 22 ጨዋታዎች ላይ መረቡን ያላስደፈረው ዴቪድ ራያ…
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ስፔናዊው የአርሰናል ግብ ጠባቂ ዴቪድ ራያ በ2025/26 በሁሉም ውድድሮች 22 ጊዜ መረቡን አላስደፈረም፡፡
ዴቪድ ራያ በ2024/25 የውድድር ዓመት ከኖቲንግሃም ፎረስቱ ማትዝ ሴልስ ጋር የፕሪሚየር ሊጉን የወርቅ ጓንት መጋራት ችሏል፡፡
በዚህ የውድድር ዓመት በሊጉ 31 ጨዋታዎች በማድረግ 15 ጊዜ ግቡን ያላስደፈረው ዴቪድ በሁሉም ውድድሮች 22 ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር አስደናቂ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል፡፡
አርሰናል ትላንት ምሽት ወደ ፖርቹጋል አቅንቶ ስፖርቲንግ ሊዝበንን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ የጫወታው ኮከብ ዴቪድ ራያ የነበረ ሲሆን÷ ድንቅ ግብ የሚሆኑ እድሎችን አምክኗል፡፡
ቡድኑ በካራባዖ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በማንቼስተር ሲቲ ዋንጫውን ሲነጠቅ እንዲሁም በአፍ ኤ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ በሳውዝ ሃምፕተን ሲሰናበት ዴቪድ ራያ በጨዋታዎቹ አልተሳተፈም ፡፡
በሁለቱ መራር ሽንፈቶች ዴቪድ ራያን በመተካት ሌላኛውን ስፔናዊ ኬፓ አሪዛባላጋን የግብ ዘብ አድርጎ የተጠቀመው ሚኬል አርቴታ በርካታ ትችቶችን አስተናግዷል፡፡
የትላንት ምሽቱ የዴቪድ ብቃት በእርግጥም የአሰልጣኝሚኬል አርቴታን ውሳኔ ሲተቹ የነበሩ ተንታኞችን ሀሳብ እውን ያደረገ እንደነበር ተመላክቷል፡፡
የብሬንትፎርድ የቀድሞ ግብ ጠባቂ አሁን ላይ የአርሰናል ወሳኝ ተጫዋች ብቻም ሳሆን በዓለም ላይ ካሉ ቀዳሚ ሶስት ግብ ጠባቂዎች አንዱ መሆኑን በርካቶች ይስማማሉ፡፡
አርሰናል የሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ ከቻለ ዴቪድ ራያ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን ÷ የውድድር ዓመቱን የወርቅ ጓንት ሊወስድ እንደሚችል መጠቆሙንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከዴቪድ ራያ በመቀጠል የኢንተር ሚላኑ ግብ ጠባቂ ያን ሶመር (18) እንዲሁም የኮሞው ግብ ጠባቂ ጂያ ቡቴዝ (17) ጊዜ በሁሉም ውድድሮች ግባቸውን ሳያስደፍሩ ይከተላሉ፡፡
በአቤል ነዋይ