19 ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘችው ኢትዮጵያ…
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከለውጡ ወዲህ ለቅርስ ልማት የተሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን ቱሪዝም ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው አሉ የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው፡፡
መንግስት በነደፈው የብዝኃ ዘርፍ ፖሊሲ አማካኝነት ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን አስችሏል ነው ያሉት፡፡
ለዘመናት የተዘነጉ በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ተገቢውን ጥገናና እድሳት አግኝተው ለጎብኚዎች ክፍት መደረጋቸውን አስታውሰው፥ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን የማልማት ተግባር በውጤታማነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ ጂማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት፣ የሐረር ጁገል ግንብ፣ ሶፍ ኡመር ዋሻን ጨምሮ በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ መታደሳቸውን አንስተዋል፡፡
በተለይም ለባህልና የከተማ ቱሪዝም ትኩረት በመሰጠቱ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸው፥ የኢትዮጵያ የቅርስ ልማት ሥራ የቱሪዝም ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው ብለዋል።
የቅርስ ቦታዎችን የማዘመን ስራ የኢትዮጵያን ገጽታ ከመገንባቱ ባለፈ የጎብኝዎችን ቁጥር በመጨመር የቱሪዝም ገቢን ማሳደጉንና ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።
የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ የኢትዮጵያን ክብርና ታሪክ ከቱሪዝም የሚያስትሳስሩ ሙዚየሞች መገንባታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ቅርሶች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ የተደረገው ጥረት ለሀገሪቱ ታሪካዊ እሴቶች ተገቢውን ክብር አስገኝቷል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 19 ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ ሥፍራ መያዟን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአገው ፈረስ ባህል፣ የሀላባ የዘመን መለወጫ ‘ሴራ’ እንዲሁም ዋዛ የሙዚቃ መሳሪያ ጨዋታ (ዙምባራ) በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ መቅረባቸውን አመልክተዋል፡፡
አስቸኳይ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ቅርሶች ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን፥ በጣና ሐይቅ የሚገኙ ደሴቶችንና የአልነጃሺ ታሪካዊ መንደርን ለማስመዝገብ የተጀመሩ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በዩኔስኮ የሚመዘገቡ ቅርሶች በባህል ላይ ያተኮሩ እንደነበር አንስተው፥ በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮ ቅርሶችን ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡