የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ዳግም ያረጋገጡ አዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች…
በኢትዮጵያ አፋር ስምጥ ሸለቆ በመካከለኛው አዋሽ የምርምር ፕሮጀክት ከ100 ሺህ ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ የጥንታዊ ሆሞ ሳፒየንስ ቅሪተ አካላት ተገኝተዋል አለ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፡፡
የባለሥልጣኑ የአጥኚ ቡድን የሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ጉዞንና ጥንታዊ የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳዩ አዳዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝቶችን ይፋ አድርጓል።
ጥናቱ በዮናስ በየነ (ዶ/ር) የተመራና ከ24 ሀገራት የተውጣጡ ሳይንቲስቶች የተሳተፉበት የብዙ ዓመታት ምርምር ውጤት መሆኑ ተገልጿል።
በጥናቱ የተገኘው መረጃ ኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም ያረጋገጠ ሲሆን÷ በአፍሪካ የሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት የነበረበትን ከ900 ሺህ እስከ 200 ሺህ ዓመታት ያለውን ጊዜ የሚዘክሩ አዳዲስ መረጃዎችን ይዟል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በወቅቱ እንደገለጹት÷ መንግሥት ለሳይንሳዊ ምርምር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ በርካታ የምርምር ሥራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
በየጊዜው እየተደረጉ በሚገኙ ምርምሮችም የተለያዩ የጥንት ግኝቶች ለዓለም እየተበረከቱ መሆኑን ጠቅሰው÷ ዛሬ ይፋ የተደረገው የምርምር ውጤት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
በምርምሩ የሆሞ ሳፒየንስ የሰው ዘር አመጣጥን፣ ሰዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ የድንጋይ መሣሪያዎችን፣ የሰው ዘር ቅሪተ አካላትንና የተለያዩ የእንስሳት ቅሪቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ አዲስ ሳይንሳዊ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች ኢትዮጵያ አሁንም የሰው ልጅ ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም ለዓለም ያረጋገጡ ክስተቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ተመራማሪው ዮናስ በየነ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷በአፋር ስምጥ ሸለቆ ሀሊቢ በተባለ ስፍራ የተገኙ ወሳኝ የአርኪኦሎጂ እና የፓሊዮአንትሮፖሎጂ ግኝቶችን የሚተነትን ሳይንሳዊ ጽሑፍ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው “ፕሮሲዲንግስ ኦፍ ዘ ናሽናል አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ” መጽሔት ላይ ዛሬ ታትሞ መውጣቱን ገልጸዋል።
በሀሊቢ አካባቢ የተደረገው ይህ ጥናት ከ100 ሺህ ዓመታት በፊት የነበረውን የሰው ልጅ አኗኗርና አካባቢያዊ ሁኔታ የሚፈትሹ አዳዲስ መረጃዎችን ይፋ ማድረጉን አስታውቀዋል።
በጥንቃቄ የተሰሩና ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውሉ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የድንጋይ መሣሪያ ስብስቦች መገኘታቸውን ጠቁመው÷ የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ እድገት በወቅቱ ምን ይመስል እንደነበር ትልቅ ማሳያ መሆኑን ተመራማሪው አብራርተዋል።
በወቅቱ አካባቢው የዛሬውን በረሃማ ገጽታ ሳይሆን ለምለምና ጫካማ እንደነበር የሚያሳዩ የጉሬዛ፣ የዝንጀሮ፣ ቀንድ ያላቸው እንስሳት፣ የአይጦች እና የአእዋፍ ቅሪቶች መገኘታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ይህም በጥንታዊው የአዋሽ ወንዝ አካባቢ የነበረውን የተመቻቸ የተፈጥሮ ሁኔታና የሰው ልጆች እንቅስቃሴ ያሳያል ነው ያሉት፡፡
ግኝቱ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን በተጨባጭ ከማረጋገጡም በላይ፣ ጥንታዊ ሆሞ ሳፒየንሶች በአፋር ስምጥ ሸለቆ የነበራቸውን የኑሮ ሁኔታ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የአካባቢ ተጽዕኖ በዝርዝር የሚያሳይ ነው።