የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ከኢትዮጵያ የልማት አጀንዳዎች ጋር የተጣጣሙ ናቸው – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በራስ አቅም እና ቴክኒካል ድጋፍ የተደረጉት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ከኢትዮጵያ የልማት አጀንዳዎች ጋር የተጣጣሙ ናቸው አሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፡፡
ኢዮብ (ዶ/ር) በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ባለው የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የ2026 ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን በተካሄደው የአቅም ግንባታ መድረክ ላይ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡
በዚህ ወቅት በኢኮኖሚ ማሻሻያ በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ አዋጅ መሰረት ተግባራዊ ስለተደረገው የወለድ ተመን፣ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ፣ የገበያ መር የምንዛሪ ተመን እና በሀገሪቱ ያለውን አጠቃላይ የፋይናንስ ቁጥጥር ስርዓት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በራስ አቅም እና ቴክኒካል ድጋፍ የተነደፉ መሆናቸውን ገልጸው÷ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው የልማት አጅንዳዎች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ገበያን ማጠናከር እና የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ በኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ የተደረጉ ጉዳዮች እንደሆኑም አንስተዋል፡፡
በሂደት ላይ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማጠናከር አስተማማኝ ተቋማዊ አቅም፣ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና የግል ዘርፍ መር ኢኮኖሚን ማጠናከር የሚችል የፋይናንስ ስርዓት መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ አጽንዖት መስጠታቸውን ባንኩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡