Fana: At a Speed of Life!

11 ግለሰቦች በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም በማዋል ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 3 ሺህ 887 ሰዎችን በህገወጥ መንገድ በማዘዋወር 4 ቢሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም በማዋል የወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ልዩ ልዩ የወንጀል ችሎት ክስ ተመሰረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ እና ለ)፣ 38 (1)  እና በሰው  መነገድ እና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 4 (2)፣ (ሀ)፣ (ሐ) እና (መ) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ወንጀል ፈጽመዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ጠቅሷል።

ተከሳሾቹ  ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሊቢያ ድረስ የወንጀል ሰንሰለት በመዘርጋት፣ ቡድን በማደራጀት እና በመምራት፣ በሰዉ ልጅ ለመነገድ የተለያዩ የስራ ክፍፍሎች በማድረግ ግለሰቦችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት በመመልመል ወደ አውሮፓ ተሻግረዉ ጥሩ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ስራዎች ላይ እንደሚሰማሩ በማሳመን፣ የጉዞ ወጪያቸውን በመሸፈን ወደ ባህርዳር እና ጎንደር በማጓጓዝ በመተማ፣ ሱዳን  በማድረግ በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገራቸው በክሱ ተዘርዝሯል።

በዚህ መልኩ ድንበር ያሻገሯቸውን ሰዎች ሊቢያ እና ሱዳን ውስጥ በማሰርና በማሰቃየት ለጉዞ የወጣ ወጪ ነው በሚል ከፍተኛ መጠን ያለው ክፍያ ከግለሰቦቹ ቤተሰቦች በመጠየቅ እና ክፍያው እስኪከፈል ድረስ ግለሰቦቹን በዕዳ መያዣነት አስረው በማስቀመጥ በሰው የመነገድ ወንጀል ሲፈፅሙ ቆይተዋል ብሏል።

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ ይትባረክ ዳዊት ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሊቢያ ድረስ የተዘረጋዉን የወንጀል ሰንሰለት እና ቡድኖችን በበላይነት የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነትን እንዲሁም ተበዳዮችን ከቦታ ቦታ የማዘዋወር፣ የዝዉዉር ሂደትን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንደነበረው በክሱ ተመላክቷል።

2ኛ ተከሳሽ ቴዎድሮስ አየነው የተዘረጋውን የወንጀል ሰንሰለት እና የቡድኑን አባላት የማስተባበር ኃላፊነትን በመያዝ ዋነኛ ጥቅም ተከፋይነት ኃላፊነት ለራሳቸዉ በመስጠት እና ከተበዳይ ቤተሰብ ገንዘብን የመሰብሰብ ተጨማሪ ኃላፊነት በመያዝ፣ ሌሎች ተከሳሾች ከተበዳይ ቤተሰብ የሚሰበሰብ ገንዘብን የመሰብሰብ እና ገንዘቡን በሰዉ ማዘዋወር ሂደት ለሚሳተፉ የቡድን አባላት ክፍያ መፈፀም እና ትርፉን በአስተባባሪዎች አዛዥነት የማስተላለፍ ኃላፊነት ይዘው እንደነበር ተብራርቷል፡፡

በተጨማሪም 2ኛ ተከሳሽ ባሰማሯቸው መልማዮች አማካኝነት ተበዳዮችን ከሚኖሩበት አካባቢ በመምረጥ ለጉዞው አሳምነዉ የመልመል፣ የማጓጓዝ፣ ድንበር የማሻገር ከዚያም በዕዳ መያዣነት አስረዉ በማቆየት አካላዊ ጉዳትን ጨምሮ በማሰቃየት ወደ ተጎጂ ቤተሰብ ስልክ በመደወል ከፍተኛ ገንዘብ የማስከፈል፣ የሚከፈለውን ክፍያ የባንክ ሂሳብ ቁጥር በመክፈት የመሰብሰብ እና በወንጀሉ ሂደት ውስጥ ለተሳተፉ ሰዎች ክፍያ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች በማዋል ገንዘቡን ለሚያስተዳድሩ ተከሳሾች የማስተላለፍ፣ እንዲሁም የተሰበሰበውን ገንዘብ ለተለያዩ ተግባራት በማዋል የማስተዳደር የወንጀል ተግባር ድርሻ ክፍፍል አድርጎ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ገልጿል፡፡

1ኛ ተከሳሽ እና በሱዳንና በሊቢያ ሀገር በስሩ ያደራጃቸዉ የወንጀል ቡድን አባላት ወደ ተጎጂ ቤተሰቦች ስልክ በመደወል ለተደረገው ጉዞ የወጣ ወጪ ነው በሚል ከ7 ሺህ 500  እስከ 12 ሺህ ዶላር ቤተሰቦቻቸው እንዲከፍሉ መጠየቁ በክሱ ተጠቅሷል።

ተከሳሹ እና ያደራጃቸዉ ገራፊዎች ተጎጂዎች ቤተሰቦቻቸው ክፍያውን ካልከፈሉ ልጆቹን በህይወት እንደማያገኟቸው በመግለፅ እያስፈራሩ ክፍያው በአፋጣኝ እንዲፈጸም የተጎጂ ቤተሰቦች ጋር ደጋግመው ስልክ በመደወል፣ ተጎጂዎችን ሲያሰቃዩ የሚያሳይ ቪዲዮ ቀርጸው መላካቸውን አመልክቷል።

በዚህም ከ2015 እስከ 2018 ዓ.ም ታህሳስ ወር ድረስ ብቻ 3 ሺህ 887 የሚሆኑ ተበዳዮችን በማገት ከቤተሰቦቻቸው 4 ቢሊየን 25 ሚሊየን 104 ሺህ 797 ብር እንዲሰበሰብ በማድረግ፣ የተሰበሰበዉን ገንዘብ በመካከላቸዉ በማዘዋወር፣ ለተለያዩ የዝዉዉር ሂደቱ ወጪዎች በመክፈል፣ ቀሪ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸዉ በማዋል እና በህገወጥ ባንክ ስራ ሂደት ከሀገር እንዲሸሽ ማደረጋቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል።

የሰዉ ልጅ በመነገድ የሰበሰቡትን ገንዘብ ከፊሉን ለራሳቸዉ አገልግሎት ያዋሉ፣ ለግብረአበሮቻቸዉ ጥቅም እንዲሰጥ ያደረጉ፣ አብዛኛዉን ገንዘብ በህገወጥ የባንክ ስራ ከሀገር እንዲሸሽ ያደረጉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ከባድ የሰው መነገድ ወንጀል ፣በወንጀል የተገኘን ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል እና በሕገወጥ የባንክ ስራ ወንጀል በድምሩ በ16 ክሶች ተከሰዋል፡:

በሲፈን መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.