Fana: At a Speed of Life!

አስደናቂ ጉዞ ላይ የሚገኘው አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ በጀርመኑ ክለብ ባየርን ሙኒክ አስደናቂ የውድድር ዓመት እያሳለፈ ይገኛል፡፡

ቤልጂየማዊው ቪንሰንት ኮምፓኒ የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው በሀገሩ ክለብ አንደርሌክት ሲሆን በተጫዋችነት ዘመኑ ለሀምበርገር እና ማንቼስተር ሲቲ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡

በማንቼስተር ሲቲ ከቆየባቸው 11 የውድድር ዓመታት ውስጥ በስምንቱ ቡድኑን በአምበልነት መምራቱ ይታወሳል፡፡

በማንቼስተር ሲቲ ምርጥ ብቃቱን ማሳየት የቻለው ቪንሰንት ኮምፓኒ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ከታዩ ምርጥ ተከላካዮች መካከል አንዱ ነው፡፡

ኮምፓኒ ከማንቼስተር ሲቲ ጋር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ ኤፍ ኤ ካፕ፣ ካራባኦ ካፕ እና የኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ በ2011/12 የውድድር ዘመን ከ44 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ሲያሳካ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን፤ በወቅቱ የሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ መመረጡ ይታወሳል፡፡

ለሀገሩ በ17 ዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገ ሲሆን፤ ከፈረንጆቹ 2004 እስከ 2019 ድረስ ለ15 ዓመታት የቤልጂየም ብሔራዊ ቡድንን በማገልገል 89 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡

ከፈረንጆቹ 2010 ጀምሮ ብሔራዊ ቡድኑን በአምበልነት ያገለገለው ኮምፓኒ በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ከሀገሩ ቤልጂየም ጋር ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አይዘነጋም፡፡

ከማንቼስተር ሲቲ የተሳካ የተጫዋችነት ዘመን በኋላ ወደ ልጅነት ክለቡ አንደርሌክት በመመለስ ለአንድ ውድድር ዓመት ተጫውቶ በፈረንጆቹ 2020 ራሱን ከእግር ኳስ ዓለም አግልሏል፡፡

ኮምፓኒ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ እግር ኳስን በጀመረበት በቤልጂየሙ ክለብ አንደርሌክት የአሰልጣኝነት ሥራውን ጀምሯል፡፡

ከአንደርሌክት በመቀጠል በርንሌይን የተረከበው አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ ቡድኑን በያዘበት በመጀመሪያው የውድድር ዓመት ከሻምፒዮን ሺፑ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማሳደግ ችሏል፡፡

አሰልጣኙ በርንሌይን ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማሳደግ ቢችልም በሊጉ መቆየት እንዳልቻለ የሚታወስ ሲሆን ቡድኑ ወደ ሊጉ ባደገበት ዓመት ወደ ሻምፒዮን ሺፑ ለመውረድ መገደዱ ይታወሳል፡፡

በ2024/25 የጀርመኑን ክለብ ባየርን ሙኒክ የተረከበው አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ በመጀመሪያው የውድድር ዓመት የቡንደስሊጋውን ዋንጫ አሳክቷል፡፡

በአሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ የሚመራው ባየርን ሙኒክ በዚህ የወድድር ዓመት በ76 ነጥብ ቡንደስሊጋውን እየመራ ሲሆን፤ በ29 የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች 105 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰው ባየርን ሙኒክ ለዋንጫው ቅድመ ግምት ካገኙ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፡፡

ባየርን ሙኒክ ለመጨረሻ ጊዜ በ2019/20 የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ያሳካ ሲሆን፤ በዚህ የውድድር ዓመት ከአሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ ጋር ለዋንጫው የሚያደርገው ጉዞ ይጠበቃል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.