Fana: At a Speed of Life!

በ9 ወራት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የውጭ ጎብኚዎችን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የውጭ ዜጎች የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች መጎብኝታቸውን የትራቭል ኤንድ ቱር ወርልድ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ድረ ገጽ የሆነው “ትራቭል ኤንድ ቱር ወርልድ” እንዳስነበበው÷ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ እያከናወነቻቸው የሚገኙ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው፡፡

አሁን ላይ ለቱሪዝም ትኩረት በመስጠት በተተገበሩ ኢኒሼቲቮች ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ መዳረሻዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኗን አስገንዝቧል፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የውጭ ጎብኚዎች በኢትዮጵያ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን እንደተመለከቱ ዘገባው አብራርቷል፡፡

ከዚህም ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን ትራቭል ኤንድ ቱር ወርልድ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴርን ዋቢ አድሮ ዘግቧል።

ውጤቱ የሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ስኬታማ ሽግግር እያደረገ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነና በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት የተደረጉ ስልታዊ የሪፎርም ሥራዎች የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ አመልክቷል፡፡

እንደ ገበታ ለሀገር ያሉ ኢኒሼቲቮች የከተሞችን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አውስቷል፡፡

በዚህም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አዳዲስ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት መዳረሻዎች መፍጠር እንደተቻለ ዘገባው ያስረዳል፡፡

ሥራዎቹ እንደ ሐረር ጁገል ግንብ እና ፋሲል አብያተ መንግሥት ያሉ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችን ከመጠገንና ከመንከባከብ ጋር ተቀናጅተው መከናወናቸው ለዘርፉ አቅም እንደሰጡ ተጠቁሟል፡፡

ከዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ከፍተኛ መነቃቃት ማሳየቱን እና ባለፉት 9 ወራት ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች 60 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ዘገባው ጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በተያዘው ዓመት ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን ማስተናገድ የተቻለ ሲሆን÷ ይህም መዲናዋ ለንግድ ቱሪዝምና ለዓለም አቀፍ ስብሰባ ዋነኛ ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ያሳያል ነው ያለው፡፡

በፈረንጆቹ 2025 በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ቁጥር ላይ የታየው የ15 በመቶ ዕድገት፣ በዓለም የጉዞ እና የቱሪዝም ምክር ቤት ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ተስፋ ሰጪ ከሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ እንድትሆን እንዳደረጋት ዘገባው አስታውሷል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያገኘ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለስኬቱ ወሳኝ ሚና መጫወቱ ተጠቅሷል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.