Fana: At a Speed of Life!

የሁሉም ባንክ ደንበኞች እስከ ግንቦት 6 የባንክ ሂሳብ ቁጥራቸውን ከፋይዳ ጋር እንዲያስተሳስሩ ማሳሰቢያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሁሉም ባንክ ደንበኞች እስከ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የባንክ ሂሳብ ቁጥራቸውን ከፋይዳ ጋር እንዲያስተሳስሩ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

ብሔራዊ ባንክ ለፋና ዲጂታል በላከው መግለጫ፤ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሚታየውን የማንነት ማረጋገጫ ክፍተት ለመሙላት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይዳ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን እንደ ቀዳሚ የማንነት መለያ መታወቂያ የመጠቀም ትግበራ መጀመሩን አስታውሷል፡፡

ነባር የባንክ ሂሳብ ቁጥሮችን ከፋይዳ ጋር የማስተሳሰር ስራ ከታሕሣሥ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ባንኮች ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሷል፡፡

ይህ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የማስተሳሰር ስራ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በከፍተኛ ርብርብ ቢከናወንም፤ ከጠቅላላው የባንክ ሂሳብ ባለቤቶች አንጻር ሲታይ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ብሔራዊ መታወቂያን ከፋይዳ ጋር ለማስተሳሰር የተለያዩ አማራጮች ይፋ መደረጋቸው ለምዝገባው ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ያለው ባንኩ፤ ደንበኞች እስከ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የባንክ ሂሳብ ቁጥራቸውን ከፋይዳ ጋር እንዲያስተሳስሩ አሳስቧል።

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በሀረር፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ አስተዳደር፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሆሳዕና፣ ወልቂጤ፣ ሸገር፣ ጅማ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ቢሾፍቱ፣ ባቱ፣ አምቦ፣ መቐለ፣ አክሱም፣ ዓዲግራት፣ ጋምቤላ እና አሶሳ ከተሞች የሚገኙ ደንበኞች የባንክ ሂሳብ ቁጥራቸውን ከፋይዳ ጋር ማስተሳሰር አለባቸው ብሏል።

በተቀሩት የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ደንበኞች ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል ነው ያለው።

በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የባንክ ሂሳብ ቁጥራቸውን ከፋይዳ ጋር የማያስተሳስሩ ደንበኞች ሂሳባቸው ከወጪ ወይም ተቀናሽ ግብይት የሚታገድ መሆኑን ገልጾ፤ እገዳው የሚነሳው የሂሳብ ቁጥሩ ከፋይዳ ጋር ሲተሳሰር ብቻ ነው ብሏል፡፡

ማሳሰቢያው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን እና በውጭ የሚኖሩ ነዋሪዎችን እንደማይመለከት ገልጾ፤ በውጭ የሚገኙ የሂሳብ ባለቤቶች አስፈላጊውን ማስረጃ ለባንኮች በማቅረብ እና በማረጋገጥ ከውሳኔው ነፃ መሆን እንደሚችል በመግለጫው አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.