አርሰናል የሊጉን መሪነት ለመረከብ …
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ34ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር አርሰናል በሜዳው ኢምሬትስ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ኒውካስል ዩናይትድን ያስተናግዳል፡፡
በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው አርሰናል ባለፉት ሦስት ዓመታት በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ያለፈው ታሪክ በዚህ ዓመት እንዳይደግም የቡድኑ እና የደጋፊዎች ትልቅ ስጋት ነው፡፡
የካራባኦ ካፕ ዋንጫን በማንቼስተር ሲቲ የተነጠቀው አርሰናል ከኤፍ ኤ ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው በሳውዛምፕተን ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ለአራትዮሽ ዋንጫ ሲፎካካር የነበረው የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ከሁለቱ ዋንጫዎች የወጣ ሲሆን በቀሪ ሁለት ውድድሮች ለዋንጫው የሚያደርገው ጉዞ ይጠበቃል፡፡
ለበርካታ ወራት ሊጉን ሲመራ የነበረው የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል አሁን የሊጉን መሪነት ለማንቼስተር ሲቲ አስረክቧል፡፡
የሊጉን መሪነት በማንቼስተር ሲቲ የተነጠቀው አርሰናል መሪነቱን ለመረከብ የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
በሊጉ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው አርሰናል ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡
ቡካዮ ሳካ እና ሪካርዶ ካላፊዮሪ ኒውካስል ዩናይትድን በሚገጥመው የቡድን ስብስብ ውስጥ እንደሚካተቱ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ገልጸዋል፡፡
ተጋጣሚው ኒውካስል ዩናይትድ በበኩሉ በሊጉ ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን ወደ አሸናፊነት ለመምጣት ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አርሰናል ሦስቱን ሲያሸንፍ ኒውካስል ዩናይትድ በሁለቱ ድል አድርጓል፡፡
ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 8 ሰዓት 30 ላይ ፉልሃም በሜዳው ክራቨን ኮቴጅ አስቶንቪላን ያስተናግዳል፡፡
አስቶንቪላ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ቦታን ለማግኘት የሚያደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ይፋለማል፡፡
በአሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬ የሚመራው አስቶንቪላ በሊጉ ተከታታይ 2ኛ ድሉን ለማሳካት ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡
በሊጉ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ያላደረገው ፉልሃም በበኩሉ ወደ አሸናፊነት ለመምጣት የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አስቶንቪላ ሁሉንም በማሸነፍ የበላይነት አለው፡፡
በሌላ የሊጉ ጨዋታ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ይጫወታል፡፡
የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ቦታን ለማግኘት እየተፋለመ የሚገኘው ሊቨርፑል በሊጉ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ተከታታይ አምስት ጨዋታዎችን አሸንፎ የነበረው ሊቨርፑል በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናገደው በ6ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር በክሪስታል ፓላስ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ክሪስታል ፓላስ ሁለቱን ሲያሸንፍ ሊቨርፑል በአንዱ ድል አድርጎ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት መውረዱን ያረጋገጠው ዎልቭስ ከቶተንሃም ሆትስፐር እንዲሁም ዌስትሃም ዩናይትድ ከኤቨርተን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ