Fana: At a Speed of Life!

በሆርሙዝ ሰርጥ እየተደረገ ባለው ክልከላ ወደ ኢራን የሚጓዙ 38 መርከቦች አቅጣጫ ቀየሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በሆርሙዝ ሰርጥ እያደረገች ባለው ክልከላ ምክንያት ወደ ኢራን ሊያልፉ የነበሩ 38 መርከቦች አቅጣጫ ቀይረዋል።

የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ዕዝ (ሴንትኮም) በሆርሙዝ የባህር ዳርቻ አካባቢ እያካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ 38 መርከቦች አቅጣጫ እንዲቀይሩ ወይም እንዲመለሱ መደረጋቸው ነው የተገለጸው።

ዕዙ ባጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል÷ ወደ ኢራን ለማለፍ ቀዘፋ ላይ የነበሩ መርከቦችን የአሜሪካ ጦር መርከቦች እና ሄሊኮፕተሮች ሲከለክሏቸውና ከመንገዳቸው ሲያስቆሟቸው ታይቷል፡፡

ክልከላው አሜሪካ የንግድ መርከቦች ወደ ኢራን ወደቦች እንዳያልፉ ለማድረግ የምታደርገው ቀጥተኛ ወታደራዊ ጫና መሆኑን የገለጸው ዕዙ÷ ኢራን ወደ ድርድር እስከምትመጣ ድረስ ዋሽንግተን የሆርሙዝ ሰርጥን አግዳ እንደምትቆይ አመልክቷል፡፡

አሜሪካ በፈረንጆቹ ሚያዚያ 13 የንግድ መርከቦች ወደ ኢራን ወደቦች እንዳያልፉ ክልከላ ያደረገች ሲሆን÷ በፓኪስታን ኢስላማባድ የተደረገው የኢራን እና አሜሪካ ድርድር አለመሳካቱን ተከትሎ ክልከላውን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡

በዚህም ምክንያት የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከቀን ወደ ቀን ጭማሪ እያሳየ በመምጣቱ ዋሽንግተን የኔቶ አባል ሀገራትን ጨምሮ ከሌሎች ሀገራት በርካታ ወቀሳ እየደረሰባት እንደሚገኝ የቮይስ ኦፍ ኤምሬትስ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በዛሬው ዕለት በነጩ ቤተ መንግስት የበይነ መረብ ስብሰባ የሚያደርግ ሲሆን÷ አሜሪካ በሆርሙዝ ሰርጥ የምታደርገው ዘመቻ ይቀጥል ወይስ አዲስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልግ በሚለው ጉዳይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.