ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት ተፈራርመዋል።
የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዳንኤል ፍራንሲስኮ ቻፖ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
ስምምነቱ የጋራ መተማመን እና ዕድገት በሰነቀ ርዕይ ላይ የተመሠረተውን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በስምምነቱ የወታደራዊ ሥልጠና፣ የከተማ ልማትና በቤት ግንባታ፣ የጤና፣ የሲቪል አቪዬሽን፣ የቱሪዝም እንዲሁም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በተለይም የዲጂታል መታወቂያና ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት ዘርፎችን ያካተቱ ታሪካዊ የመግባቢያ ሰነዶች ተፈርመዋል።
እነዚህ ስምምነቶች ከፖሊሲ ሰነድነት ባለፈ ለጋራ ብልጽግና ተጨባጭ መንገዶችን የሚቀይሱ መሆናቸው ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ባለበት በዚህ ወቅት ሀገራችን የደረሰችበትን ልምድና እውቀት ለአፍሪካውያን ወንድሞቿ ለማካፈል ያላትን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ በመሰል አጋርነቶች በጋራ ለመማርና ለማደግ ዝግጁ መሆኗንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል።