በለውጡ ዓመታት ለባህልና ስፖርት ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል – ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለባህልና ስፖርት ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል አሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፡፡
“የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ ሐሳብ ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ ዘርፍ የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች በሚቀርቡበት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
ሚኒስትሯ በመድረኩ ላይ በባህል እና ስፖርት ዘርፍ በለውጡ ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ስኬቶች አብራርተዋል።
ከለውጡ በፊት ዘርፉ ለአደባባይ ክብረ በዓላት ትኩረት ማነስ፣ ባህላዊ የፍትህና ዳኝነት ስርዓትን አለመጠቀም፣ የአካታችነት እንዲሁም የባህል እሴቶችን ለአንድነት አለመጠቀም ችግር እንደነበር አንስተዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት ለነዚህ ክፍተቶች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ዘርፉ ወሳኝ ለውጥ እንዲያስመዘግብ መደላድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
በዚህም ለ83 ክብረ በዓላት እውቅና መስጠት፣ 36 አዲስ ባህል ማዕከላት መገንባት፣ ዲጂታል የቅርስ መረጃ አያያዝ ስርዓት መዘርጋት፣ የባህልና የብዝኃ ልሳን ፖሊሲ ትግበራና ተጨማሪ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች ከተገኙት ስኬቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የቤተ መጻሃፍት ግንባታና የንባብ አገልግሎት መበራከታቸውን ገልጸው፥ የብዝሃ ልሳን ፖሊሲ መተግበርና የሙያ ማህበራት ማደራጀት እንዲሁም ዘርፉን ለዲፕሎማሲ ስኬት መጠቀም ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በስፖርቱ ዘርፍ አደይ አበባን ጨምሮ 17 ሺህ 636 አዳዲስ ስታዲየሞችና የስፖርት ማዘውተሪያዎች ግንባታ የዘርፉ ትልቅ እመርታዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡