Fana: At a Speed of Life!

ከሸማችነት ወደ ምርታማነት …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎቿን ኑሮ ለማሻሻል በጀመረችው ጉዞ የከተማ ግብርና አዲስ ተስፋ ሆኖ ብቅ ብሏል።

“ምግቤን ከጓሮዬ” ንቅናቄን ተከትሎ ከተሞች ፍጆታቸውን ሙሉ በሙሉ ከመሸመት በመላቀቅ የተወሰነውን ምርት አምርተው መጠቀም ጀምረዋል።

ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት በትላልቅ እርሻዎች ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ዜጋ መኖሪያ ቤት ጭምር መጀመር እንዳለበት ያስገነዘበ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚያነሱት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል የሚደረገው ትግል “የሁላችንም የቤት ስራ” ነው።

ይህን ሀገራዊ አቋም ወደ ተግባር ለመለወጥ ደግሞ የከተማ ግብርና አንደኛው ትልቅ መፍትሄ ሆኗል።

አሁን ላይ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች ዜጎች ኮሪደሮችንና በረንዳዎችን ጨምሮ ያላቸውን አነስተኛ ቦታ በመጠቀም ለምግብነት የሚውሉ የግብርና ውጤቶችን ማምረት ጀምረዋል።

ይህ እንቅስቃሴ ከልምድ አልፎ የቤተሰብን ቀለብ የሚደጉም፣ የኑሮ ውድነት ጫናን የሚቀንስ እና ጤናማ አመጋገብን የሚያሰፍን ማህበራዊ ንቅናቄ ሆኗል።

በተለያዩ ቁሳቁሶች እና በጥቂት ቦታ ላይ ብዙ ምርት በሚሰጡ ዘዴዎች የሚከናወነው ይህ የከተማ ግብርና፣ ከተሞችን ከፍጆታ ማዕከልነት ወደ ምርት ምንጭነት እየቀየራቸው መሆኑ ለዋጋ መረጋጋት ዓይነተኛ ድርሻ አለው።

ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገርም ለከተሞች ውበትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጠው ጥቅም የጎላ ነው።

በአነስተኛ ቦታዎች ላይ የሚለሙ ተክሎች ነዋሪው በራሱ ጥረት ያመረተውን ምርት ለምግብነት ሲጠቀም የሚሰጠው ስነ-ልቦናዊ እርካታ ወደር የለውም።

በአጠቃላይ የከተማ ግብርና ከሸማችነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ጉዞ ለማጠናከር ያለው ሚና የጎላ ነው።

በዚህም በቅርቡ የግብርና ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ሥራ ላይ የነበረውን የከተማ ግብርና ስትራቴጂ በመከለስ ዘርፉን በይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እየሰራበት ይገኛል።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.