ኢትዮጵያ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሰፊ ሥርዓታዊ ሽግግር አድርጋለች – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሰፊ ሥርዓታዊ ሽግግር አድርጋለች አለ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ”የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ ቃል በማህበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች የቀረቡበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ ዘርፎች የተመዘገቡ ወሳኝ ስኬቶች ቀርበዋል።
በስምንት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ በመሰረታዊና ማህበራዊ ዘርፎች የተስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሰፊ ሥርዓታዊ ሽግግር ማድረጓ ተመላክቷል፡፡
በትምህርት ዘርፍ አዲስ ሥርዓተ ትምህርትን በመተግበር የመማሪያ መጽሐፍት ስርጭትን በማሻሻል እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርትና የሀገር አቀፍ ፈተና ሥርዓቶችን በማዘመን የትምህርት ዘርፉ ጥራትና ተዓማኒነት እንዲላበስ መደረጉ ተገልጿል።
በተመሳሳይ የጤናው ዘርፍ ለ30 ዓመታት የቆየውን ፖሊሲ በመከለስ ከመከላከል ጎን ለጎን አክሞ የማዳን አገልግሎት ላይ በትኩረት መሰራቱ ነው የተገለጸው፡፡
በዲጂታል ጤና፣ በሀገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጭና በጤና ዲፕሎማሲ ረገድ ጉልህ ውጤት ተመዝግቧል ነው የተባለው፡፡
የኢኮኖሚና ማህበራዊ አቅምን የመገንባት ስራዎችም በተመሳሳይ መልኩ ውጤታማ መሆናቸው ተጠቅሷል።
የሥራና ክህሎት ዘርፉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን (TVET) በማዘመንና የቢዝነስ ማጠናከሪያ ማዕከላትን ማስፋፋት፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ከ19 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉ ተጠቁሟል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ 26 ነጥብ 8 ሚሊየን ሴቶችንና 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ወጣቶችን በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ተሳትፎ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለተጋላጭ ዜጎችና በአደጋ ለተጎዱ ወገኖች የተሻለ ጥበቃ ማድረግ መቻሉ ተመላክቷል፡፡
በባህልና ስፖርት ዘርፍ የሀገሪቱን ቅርሶች ለብሔራዊ አንድነትና ለዲፕሎማሲ ስኬት እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቱ ተገልጿል።
ከእነዚህም መካከል 83 የአደባባይ ክብረ በዓላት እውቅና ማግኘታቸው፣ 36 የባህል ማዕከላት መገንባታቸው እንዲሁም አደይ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ ከመቶ ሺህ በላይ አዳዲስ የስፖርት መሠረተ ልማቶች መገንባታቸው የዘርፉ ጉልህ ስኬቶች መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
በአጠቃላይ በዘርፎቹ የተመዘገቡ ለውጦች መንግሥት ለተቋም ግንባታ፣ ለዲጂታል ሽግግርና ለሰው ሀብት ልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡