የቻይና ባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እያሳደገ የሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የቻይና ባለሃብቶችን የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እያሳደገ ነው አሉ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ።
አምባሳደር ቼን ሃይ ኢትዮጵያ እና ቻይና ታሪካዊና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ግንኙነታቸውም የልማት ትብብርን በማጎልበት የሀገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት እያጠናከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሀገራቱ የሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት ስትራቴጂክ አጋርነት ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ የጋራ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚሰማሩባቸው አዳዲስ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎችም ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የቻይና አልሚ ባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት በራስ መተማመን በማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የፈጠረው የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢም አዳዲስ ዕድሎችን መጠቀም የሚሹ በርካታ የቻይና ባለሃብቶችን እየሳበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የኢትዮ-ቻይና የኢኮኖሚ ትብብርም በግብርና፣ ኢንዱስትሪና የሰው ሃብት ልማት ሶስት ወሳኝ ምሰሶዎችን ማዕከል በማድረግ በስፋት እየተሰራበት መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፈጣን የልማትና የዕድገት አቅጣጫ የሀገራቱን ስትራቴጂክ አጋርነት በማጠናከር ከፍተኛ አቅም መፍጠሩንም ገልጸዋል።
የቻይና ባለሃብቶች የኢትዮጵያ የንግድና የአምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ የኢኮኖሚ ልማትና ሽግግርን በማፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሀገራቱ በሰው ሃብት ልማት ትብብር የአዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በክህሎት የበለፀጉ ዜጎችን በማፍራት ወሳኝ ሚና እየተወጣ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በሚቀጥሉት ዓመታትም የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ስትራቴጂክ አጋርነት የበለጠ በማጠናከር የሁለትዮሽ ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።