Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ መድረክ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ ሥራዎችን እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተፈላጊነቷን የሚያሳድግና ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እያከናወነች ነው አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፥ ባለፉት ሳምንታት የቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሞዛምቢክ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎች በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

መሪዎች በጉብኝታቸው ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ በአረንጓዴ አሻራና ከፍተኛ ዕድገት ባስመዘገበችባቸው ዘርፎች ላይ ልምዷን ለማካፈልና በትብብር ለመስራት የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረሟንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የፖርቹጋል፣ የባንግላዲሽ እና ኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጉብኝት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የምታራምደውን አቋም በሚገባ ማንጸባረቅ ችላለች ነው ያሉት፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በስዊድንና ኖርዌይ ባደረጉት ጉብኝት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ ከኩባንያ አመራሮች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት በተለይ በታዳሽ ኃይል፣ ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችላትን ዲፕሎማሲያዊ ስራ ማከናወኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነቷን በሚገባ እየተወጣች ትገኛለች ነው ያሉት፡፡

እንደ አፍሪካ የሆርሙዝ ሰርጥ ጉዳይ ምክክር እንዲደረግበት አጀንዳ ማቅረቧን ጠቅሰው፥ በሌሎች አሕጉራዊ የሰላምና ደሕንነት ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳቧን ማጋራቷንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ያከናወነቻቸው የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ተግባራት ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ መሆናቸውን ገልጸው፥ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀባይነቷን እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል።

በአለምሰገድ አሳዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.