Fana: At a Speed of Life!

ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት እራስን ለመቻል በቁርጠኝነት መስራት ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት እራስን ለመቻል በዘርፉ የተጀመረውን ሥራ ይበልጥ ማጠናከር ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኘውን “ጎበዝ ሶላር ሴል” ማምረቻን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በግል ባለሃብት የተገነባው ሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በርካታ አልሚዎችን የሚያሳትፉ 30 ሼዶች እንዳሉት አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢኮኖሚ ዞኑ የግል ዘርፉ በኢንዱስትሪ መስፋፋት ላይ ያለውን ሚና አጉልቶ እንደሚያሳይ አውስተዋል፡፡

ከአጎዋ ነጻ የንግድ ተጠቃሚነት ሥምምነት እግድ በኋላ በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ላይ መሰረት ያደረጉ አምራቾች መደነቃቀፍ አሳይተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ፋብሪካዎች በሌሎች ምርቶች እንዲሰማሩ መደረጉን ጠቁመው ÷ በዚህ መሰረትም ሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሶላር፣ የኤሌክትሪክ ባጃጅ፣ ጫማዎች፣ አልባሳትና ሌሎች ምርቶችን እያመረተ ይገኛል ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ የሚገኘው ጎበዝ ሶላር ሴል ማምረቻ በመጀመሪያው ምዕራፍ 2 ጊጋ ዋት ዓመታዊ የማምረት አቅም አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ 2ኛው ምዕራፍ በቅርቡ እንደሚጀመር አመልክተዋል፡፡

የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ አብዛኛውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የተጀመረው ጥረት ስኬታማ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

አሁን የተገኘው ውጤት አስደናቂ ነው፤ ቬትናም ያየነውንና የተደመምንበትን ሥራ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ማድረግ ችለናን፤ በቀጣይ ማስፋቱ ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በአዲስ አበባ የሚገኝ በመሆኑ ብዙ የውጭ ኢንቨስተሮችን የመሳብ እድል እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሥራ እድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪንና የእውቀት ሽግግርን ጨምሮ በብዙ መልኩ በኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ሚና እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሚቀሩ ሥራዎችን ነቅሰን በመለየት በቁርጠኝነት እየሰራን ከሄድን በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ እራሷን የመቻል እድል እንዳላት አስገንዝበዋል፡፡

በርትተን ከሰራን፣ ጀምረን በሚገባ ከጨረስን እና ክፍተት እያዩ መሙላትን ካጠናከርን ተከታታይ እድገት በማምጣት የምናስበውን ውጤት ማስመዝገብ እንችላለን ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቀጣይ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ የሁላችንም ዋና ተግባር ሊሆን ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.