በኢንዱስትሪ የበለጸገችና ራሷን የቻለች ጽኑ ኢትዮጵያን እንገነባለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጋራ በመሆን ለሚመጣው ትውልድ ጸኑ፣ በኢንዱስትሪ የበለጸገችና ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን እንገነባለን አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ውጤት ተኮር አመራራችን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ተንጸባርቋል ብለዋል።
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ላይ የሀገራዊ ርዕያችንን ተጨባጭ ስኬት መመልከታችን ትልቅ ክብር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም በአራት ዓመታት ተከታታይ ጥረት የተገኘ የሚጨበጥ ውጤት መሆኑን አውስተዋል፡፡
በዚህም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አማካይ የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማድረጉን ገልጸው፥ ባለፉት አራት አመታት ከ2ሺህ 800 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ በሀገር ውስጥ ተኪ ምርት ከ4 ነጥብ 85 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን አመልክተዋል፡፡
ዛሬ የተከፈተው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከመላው ሀገሪቱ የተወጣጡ ንቁ አምራቾችንና ስታርትአፖችን በጨመረ ዐቅም በአንድነት ያሰባሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ታላቅ የነበርን ነን ይበልጥም ታላቅ እንሆናለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጋራ በመሆን ይህንን ጠንካራ መነቃቃት በማስቀጠል ለሚመጣው ትውልድ ጸኑ፣ በኢንዱስትሪ የበለጸገችና ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን እንገነባለን ሲሉ አረጋግጠዋል።