Fana: At a Speed of Life!

በመሠረተ ልማት ዝርጋታ የገጠሩን ማሕበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል- የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመሠረተ ልማት ዝርጋታ የገጠሩን ማሕበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል አለ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በመሠረተ ልማት ዝርጋታ የገጠሩን ማሕበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ባለፉት ስምንት ዓመታት መንግሥት በመንገድ፣ በመስኖና በውሃ ዘርፎች ላይ ባደረገው ከፍተኛ የበጀት ድልድል የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ለማሻሻል ሰፊ ሥራዎችን አከናውኗል።

በመንገድ ዘርፍ በ2010 ዓ.ም የነበረው የ126,773 ኪ.ሜ ሽፋን በስምንት ዓመታት ውስጥ ወደ 180ሺህ 232 ኪ.ሜ በላይ አድጓል።

ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ53ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶች ተገንብቶ ለሀገሪቱ ልማት ዉሏል ማለት ነው፡፡ ከለውጡ በፊት የነበረው አንድ የፍጥነት መንገድ ብቻ ሲሆን፣ አሁን ግን የሞጆ-አርሲ ነገሌ እና የድሬዳዋ-ደዋሌ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያን የ1,600 ኪ.ሜ የፍጥነት መንገድ ባለቤት ለማድረግ አራት አዳዲስ ፕሮጀክቶች በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

በመስኖ ልማት እንደ ተንዳሆ፣ የቆጦ፣ሪቡና መገጭ ያሉ ግድቦችን ጨምሮ በርካታ አነስተኛና መካከለኛ ፕሮጀክቶች በመገንባታቸው አርሶ አደሩ በዓመት ደጋግሞ እንዲያመርት አስችለዋል።

ይህም ከ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንዲለማ በማድረግ ኢትዮጵያ ስንዴን ወደ ውጭ ኤክስፖርት እንድታደርግ መሠረት ጥሏል።

የንጹሕ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ በለፉት 6 አመታት በኢትዮጵያ ግዙፍ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል ።

ከእነዚህም መካከል የሎጊያ ፣የጎዴ፣የለገዳዲ ምዕራፍ 2 የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት፣ የአንጀሌ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የዳሊፋጌ ባለ ብዙ መንደር ፕሮጀክት እና የሁርሶ የውሃ ፕሮጀክት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም የአይሳኢታ እና አፋምቦ፣ የገነቴ፣ የአከር እንዲሁም የጎሮ-ጫንጮ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የበቁ ሲሆን፣ እነዚህ ሥራዎች በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች የሚስተዋለውን የውሃ እጥረት በመቅረፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።

እነዚህ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የሀገር ውስጥ የቴክኒክ አቅምን አጠናክረዋል።

የቢሊዮኖች ሀብት የፈሰሰባቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ መጠበቅና መንከባከብ የሁላችንም ኃላፊነት ነው።

መንግሥትም መሠረተ ልማቶችን ወደ ራቅ ያሉ አካባቢዎች የማስፋፋትና ያሉትን የማዘመን ሥራውን በትኩረት ይቀጥላል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.