በኦሮሚያ ክልል ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማሰራጨት…
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለመኸር እርሻ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
የቢሮው ም/ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በክልሉ በዘንድሮው መኸር እርሻ 11 ነጥብ 1 ሚሊየን ሔክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም ምርታማነትን የሚያሳድጉ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ በተገቢው ሰዓት ለማዳረስ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ለ2018/19 ምርት ዘመን መኸር እርሻ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ድረስም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አመልክተዋል፡፡
ቅድሚያ ለሚዘሩ የሰብል አይነቶች ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በምርጥ ዘር ሥርጭት ሒደት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል በክልል ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ በተዋረድ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
አርሶ አደሮች እውቅና የሌላቸውና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርጥ ዘሮች መጠቀም እንደሌለባቸው አሳስበው ÷ ሕገ ወጥ ተግባራትን ሲመለከቱም ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ