ሚያዝያ 27 የታሪክ ማኅደር ተገልጦ የሚነበብበት የትናንት ትዝታ ብቻ አይደለም – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚያዝያ 27 የታሪክ ማኅደር ተገልጦ የሚነበብበት የትናንት ትዝታ ብቻ አይደለም አለ።
አገልግሎቱ 85ኛውን የአርበኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፈው መልዕክት፤ አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው ሀገርን ጠብቀው የማቆየት ታሪካዊ ግዴታቸውን በድል ተወጥተዋል ብሏል።
እነርሱ በነፃነት ያቆዩልንን ሀገር እኛ በዕውቀታችን፣ በላባችንና በሥራችን የመገንባት የዘመኑ አርበኝነት አደራ አለብን ሲል አስገንዝቧል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
ሚያዝያ 27 ለእኛ የታሪክ ማኅደር ተገልጦ የሚነበብበት የትላንት ትዝታ ብቻ አይደለም፤ የአርበኞች አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን የድል መንፈስ እንደ ብዕር በመጠቀም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጻፍ የጀመርንበት የትንሣኤ ጉዟችን መነሻ መሠረት ነው! ሚያዝያ 27 የነፃነት ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን፣ ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን በክብር ለመረከብ ላቡን የሚያፈስበትና ያለውን የሚሰጥበት የቁርጠኝነት ቀን ነው።
ከ85 ዓመታት በፊት አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው ሀገርን ጠብቀው የማቆየት ታሪካዊ ግዴታቸውን በድል ተወጥተዋል። ዛሬ የታሪኩ ምዕራፍ ተቀይሮ ተረኝነቱ የእኛ ሆኗል፤ እነርሱ በነፃነት ያቆዩልንን ሀገር እኛ በዕውቀታችን፣ በላባችንና በሥራችን የመገንባት የዘመኑ አርበኝነት አደራ አለብን።
አባቶች በጠመንጃ ሀገር ጠበቁ፤ እኛ በቴክኖሎጂ ሀገር እንገነባለን። አባቶች ዳር ድንበር አስከበሩ፤ እኛ ድህነትን አሸንፈን ብልጽግናን እናረጋግጣለን። አባቶች ለነፃነት ወደቁ፤ እኛ ለታላቅነት እንቆማለን። ይህ የትውልድ ቅብብል ነው ። ያለ አባቶች ጥበቃ ዛሬ የምንገነባት ሀገር ባልኖረች ነበር፤ ያለ እኛ ግንባታም አባቶች የጠበቋት ሀገር ትርጉም ያለው ሕይወት ለዜጎቿ መስጠት አትችልም። በመሆኑም ትናንት በጀግንነት የተረከብናትን ሀገር፣ ዛሬ በሥልጣኔ አንጸን ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ የሞራል ዕዳ፣ የሀገር አደራ አለብን።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊያን ከስንዴ ልመና ለመላቀቅ ወገባችንን አጥብቀን፣ ማረሻችንን ጨብጠን የተነሳነው፣ ለዚህ ነው አለም እኪደመም ተደምረን 48 ቢሊዮን ችግኝ የተከለነወ፣ ለዚህ ነው ከመቀነታችን ፈትተን፣ ከጉርሳችን ቀንሰን ህዳሴያችንን እውን ያደረግነው፣ ለዚህ ነው የዘመናት የጉስቁልና ምልክት የነበሩ ያረጁ ከተሞቻችንን ለመለወጥ እያመመን የበረታነው፣ ለዚህ ነው የከረሙ ስብራቶቻችንን ለመጠገን እንመካከር ያለነው፣ ለዚህ ነው ዙሪያው ተቸንክሮብን እስከመቼ እንኖራለን ያልነው! ለዚህ ነው የታዳሽ ሀይል መሠረት ለመጣል እየተጋን ያለነው ፣ ለዚህ ነው የአፍሪካ ትልቁን የአቬሽን ማዕከል እየገነባን ያለነው አደራ ስላለብን፣ ሀገርን በላብ የማሻገር አደራ!
በመሆኑም በዚህ ታሪካዊ ቀን፣ እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ ለሀገሩ ጡብ የሚደረድር የራሱ ዘመን አርበኛ መሆን ይጠበቅበታል። ዛሬ እኛ የምናከናውናቸው የልማት ሥራዎች፣ የምናሳየው ጽኑ አንድነትና ዳር የምናደርሳቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሀገርን ጠብቀው ላቆዩን አባቶች የምንሰጠው ትልቁ የክብር መግለጫና የታሪክ ምላሻችን ነው።
ክብር ሀገርን ጠብቀው ላቆዩን አባቶች!
በትጋት ሀገርን ለሚገነቡ ልጆች!
ኢትዮጵያ በላባችን ታላቅ ትሆናለች!