Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሱዳን መንግሥት የተሰነዘረባትን ክስ ውድቅ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሱዳን መንግሥት የተሰነዘረባትን መሰረተ ቢስ ክስ ውድቅ አደረገች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የሱዳን መከላከያ ኃይል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ላይ ያቀረቡት ክስ መሰረተ ቢስ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት አንዳንድ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በመጣስ የሚደርጉትን ትንኮሳ ለህዝብ ይፋ ከማድረግ መቆጠቡን አንስቷል፡፡

የሱዳን ጦር የህወሃት ቅጥረኛ ወታደሮችን በእርስ በርስ ጦርነቱ ውስጥ ማሳተፉን እና ለእነዚህ ቅጥረኛ ወታደሮች  የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በምዕራብ ኢትዮጵያ ትንኮሳ እንዲፈፅሙ ማድረጉን ጠቅሷል፡፡

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የህወሃት ቅጥረኛ ወታደሮች በግልፅ ሲንቀሳቀሱ መታየታቸው ሱዳን ለተለያዩ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች መናኸሪያ ሆና እያገለገለች መሆኗን የሚያሳይ ታማኝ መረጃ ነው ብሏል፡፡

መሰል ድርጊቶች እና ቀደም ሲል በሱዳን ጦር እና ባለስልጣናት የተሰነዘሩ ውንጀላዎች እኩይ አጀንዳዎችን ለማራመድ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎችን ዓላማ ለማሳካት ያለመ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሱዳን ህዝቦች ጋር አጋርነቷን እና ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ ትቀጥላለች ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ÷ ኢትዮጵያ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በውይይት ይፈታል ብላ እንደምታምን አስገንዝቧል፡፡

በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሱዳን የሲቪል መንግሥት እንዲመሰረት፣ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እንዲሁም ነጻ፣ ሁሉን አቀፍ እና ግልጽ ሲቪል መር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው ብላ እንደምታምን አብራርቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.