Fana: At a Speed of Life!

ነጻ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለሀገር ሰላምና ጠንካራ ኢኮኖሚ…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለሀገር ሰላምና ለጠንካራ ኢኮኖሚ መሰረት ነው አሉ ምሁራን፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የስነ አስተዳደር ምሁራን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለጋራ እድገትና ልማት መረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙላለም ኃይለማሪያም የህዝብን ፍቃድ መሰረት ያደረገ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በተግባር ሲገለጥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን እንዳሚያመጣ አስረድተዋል፡፡

በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመሰረተ መንግስት በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት እንደሚኖረው ገልጸው፥ ዜጎች ሰላማቸው ተጠብቆ ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ ያግዛል ነው ያሉት።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የስነ አስተዳደር መምህር ፍቃዱ ቶሎሳ (ዶ/ር) እንደሚሉት፥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለጋራ የሀገር እድገትና ልማት መረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው፡፡

በዓለም የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ምሳሌ ተደርገው የሚጠቀሱ ሀገራት ቀጣይነት ያለው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ከምርጫ በኋላ የህዝብን ድምጽ ያከበረ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማድረግ የዲሞክራሲ መገለጫ ነው የሚሉት ደግሞ የስነ ዜጋና የስነ ምግባር መምህር የሆኑት ሁስማን ቃሲም ናቸው፡፡

ህዝቡ በመረጠው መተዳደር ሲጀመር ሀገራዊ ሰላም እንደሚረጋገጥና የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚፈጠር ነው የገለጹት።

ህብረተሰቡ ሰላማዊ ምርጫ ለዲሞክራሲ መሰረት መሆኑን ተረድቶ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በድምጹ ፍትሐዊ አስተዳደር በማጽናት ለሀገር ልማትና እድገት መሰረት የማኖር ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ምሁራኑ አስገንዝበዋል፡፡

በወርቅአፈራው ያለው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.