የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገሪቱ የማምረት አቅም እንዳላት የሚያሳይ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢትዮጵያ በራሷ የምትተማመን እና የማምረት አቅም ያላት ሀገር መሆኗን የሚያሳይ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።
4ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የጎበኙት ፕሬዚዳንት ታዬ÷ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለአንድ ሀገር የእድገት ደረጃ ዋልታ እና መደላድል መሆኑን ገልጸዋል።
በኤክስፖው የቀረቡ ምርቶች በራሳችን ወጣቶች የተመረቱ መሆናቸው አስገራሚ ነው ብለዋል።
የማምረት አቅም ወደላቀ ደረጃ መድረሱን የሚያሳዩ እና ከሀገር አልፎ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገሪቱ ያላትን የአምራችነት ደረጃ ከፍ የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች እና ሚሲዮኖች ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በኤክስፖው ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ አምራቾች እና ስታርትአፖች እየተሳተፉበት ይገኛል።
“ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሐሳብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 25 የተከፈተው አራተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በነገው እለት ይጠናቀቃል።
በዙፋን ካሳሁን