Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ የተፅዕኖ ድምፅ የሆነው ማህበራዊ ሚዲያ የአፍሪካውያንን ተስፋ እንዲያሳይ …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ አህጉራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚወሰድ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው አሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፡፡

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመጀመሪያው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS-2026) እየተካሄደ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ”ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ” በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

አቶ ሰይፈ ደርቤ በመድረኩ እንዳሉት፤ ጉባኤው የአህጉሪቱን የዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።

የፐልስ ኦፍ አፍሪካ መወለድ መነሻ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርቆ አሳቢ ራዕይ መሆኑን አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካ የራሷ ድምጽ እንደሚያስፈልጋትና የራሷን ታሪክ በራሷ ልጆች መተረክ እንዳለባት ባስቀመጡት መሰረት፣ ተቋሙ እውነተኛ አፍሪካዊ ትርክቶችን ለማሰራጨት በግልጽ ተልዕኮ መመስረቱን ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ ከ30 በላይ በሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ተደራሽነቱን ማስፋቱንና ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸው፤ በፍጥነት እያደገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ይህ ጉባኤ አህጉራዊ ተፅዕኖን ለማሳደግና ለማነቃቃት ያለመ መሆኑንም አብራርተው፤ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተዕፅኖ ዘመኑን በዋጀ አዲስ ዕይታ ሊበየን እንደሚገባው አንስተዋል።

ለዚህም በዓላማና በኃላፊነት የሚመራ እንዲሁም ውጤት የሚያመጣ ሊሆን እንደሚገባው አፅንኦት ሰጥተዋል።
የዲጂታል ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የአፍሪካን ትርክት ለመቀየር ቁልፍ ሚና እንዳላቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የዲጂታል ተጽዕኖን ለማዝናናት ብቻ ሳይሆን ለማስተማር፣ አንድነትን ለማጠናከርና አህጉሪቱን ለመገንባት መጠቀም እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡

የሴቶችን መሪነት የሚያጎላና ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት፣ ብዝበዛና በደል የሚቃወም የዲጂታል ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ አብሮነትን፣ የትውልዱን ተስፋና ዕድሎች አጉልተው የሚያሳዩ ትርክቶችን ማስፋት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካን ታላቅነትና ባህል በማስተዋወቅ ወጣቱን ትውልድ ለፈጠራና ለልማት ማነቃቃት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ይህንን አዲስ ንቅናቄ የሰው ዘር መገኛ፣ የአፍሪካ መዲና እና የአህጉሪቱ የጽናት ምልክት ከሆነቸው ሀገር-ኢትዮጵያ መጀመር እንደሚገባም ነው ያነሱት።

ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ያላቸውን ተቀባይነት በጥበብ፣ በድፍረት እና ለአፍሪካ ባለ ጥልቅ ፍቅር መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካውያን የራሳቸውን ታሪክ እንዲተርኩ ላደረጉት እገዛና ለአህጉሪቱ እድገት ላላቸው ቁርጠኝነት ታላቅ አክብሮታቸውን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.