የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአፋህድ አባላት ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሰላም አማራጭን ከተከተሉ 153 የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) አመራር እና አባላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለሶስት ቀናት ተወያይቷል።
በአማራ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአፋሕድ አመራርና አባላት በቅርቡ ከክልሉ መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት መፈፀማቸው ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም ድርጅቱን ወክለው 17 የአጀንዳ ሀሳቦችን ለይተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) በተደረገው ውይይት ጥልቅ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማሥፈን የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች የሰላም አምባሳደር የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸት እየተሠራም ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ኃይሎች አሁንም አጀንዳዎቻቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።
በምንተስኖት ሙሉጌታ