ጋዜጠኞች ሙያቸውን እና ሕግን እንዴት መከተል እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጋዜጠኞች ሙያቸውን እና ሕግን እንዴት መከተል እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ”የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በሚዲያ ዘርፍና ተቋማት ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች ላይ የሚመክር መድረክ ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚዲያው ዘርፍና ተቋማት ዙሪያ ያላቸውን ሀሳብ ለመድረኩ አጋርተዋል፡፡
በዚህም ከለውጡ ማግስት የመገናኛ ብዙኃን የሀሳብ ነፃነት እንዲከበር እና በሙያቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ መደረጉን አስታውሰዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን ለማረጋገጥ የተዘጉ ሚዲያዎች እንዲከፈቱ እንዲሁም የተከለከሉ ሚዲያዎች እና ጋዜጠኞች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ እና አሳሪ ሕጎች እንዲሻሻሉ መደረጉን አውስተዋል፡፡
ነገር ግን የለውጡ መንግሥት በሚዲያው ዘርፍ አበረታች ርምጃዎችን ቢወስድም ጋዜጠኞች ነፃነትን ማስተዳደር ባለመቻላቸው በርካታ ችግሮች ተከስተዋል ነው ያሉት፡፡
ሚዲያው ክፍት እንዲሆን ከተደረገ በኋላ በቀላሉ ወደ ኢንዱስትሪው ለመግባት የተቸገሩ የመገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ጋዜጠኞች ሙያቸውን እና ሕግን እንዴት መከተል እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል ብለዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ