በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በተሰራ ስራ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
”ትምህርት የበለጸገች ሀገርን እውን ለማድረግ የትውልድ ምንጭ ነው” በሚል መሪ ሀሳብ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ 33ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በቢሾፍቱ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህ ረገድ በተሰሩ ስራዎች መምህራን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸው፥ የክልሉ መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የትምህርት ጥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ትውልድን ለማፍራት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በኦሮሚያ ክልል በዚህ ወቅት 12 ነጥብ 4 ሚሊየን ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ መገኘታቸው ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አፋን ኦሮሞን የቴክኖሎጂ ቋንቋ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው ከዚህ በላይ ስኬት ለማስመዝገብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በእዮናዳብ አንዱዓለም