Fana: At a Speed of Life!

የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችን ዳር ለማድረስ እንሰራለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን ዳር ለማድረስና የሀገሪቱን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ እንሰራለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ በስድስት ክፍለ ከተሞች የተገነቡ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሕንጻዎችን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡

በተጨማሪም የፓርቲውን ደጋፊዎች በማስተባበር የተገዙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለሁሉም ክፍለ ከተሞች ተበርክተዋል።

ከንቲባ አዳነች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ጽ/ቤቶቹ በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች አስተዋጽኦ እንዲሁም የፓርቲ አመራሮችና ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በመለገስ የተገነቡ ተቋማዊ ሀብቶች ናቸው ብለዋል።

ፓርቲው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት አሰባሳቢ ትርክቶችንና እሳቤዎችን ማስረጽ የሚያስችል ተቋማዊ ግንባታን እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከእሳቤያችን በመነሳት ብዝሃነትን በማክበርና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ከሁሉም፣ በሁሉም፣ ለሁሉም የሆነች ሀገርን ለመገንባት አሁንም በትጋት እንሠራለን ነው ያሉት።

ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ መንግሥት መሠረት መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፥ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የፓርቲ መዋቅሮችን በየደረጃው የማጠናከር ሥራ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝብ ተጨማሪ ዕድል እንዲሰጠን ስንጠይቅ የጀመርናቸውን የሀገረ መንግሥት ግንባታና የአሰባሳቢ ትርክት ሥራዎች ለማጠናቀቅ ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን ዳር ለማድረስና የሀገራችንን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና የሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠበት እንዲሁም አካታችና አሳታፊ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና አባላት በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.