Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቋሚ የሁለትዮሽ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቋሚ የሁለትዮሽ የምክክር ማዕቀፍ ስምምነት በዋሽንግተን ዲሲ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን ከኢትዮጵያ ወገን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) እና ከአሜሪካ ወገን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አሊሰን ሁከር ፈርመዋል።

በስምምነቱ ኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩ የጋራ ትግበራ የሚሹ የትብብር አድማሶችን በማስፋት በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።

የተፈረመው የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር በየዓመቱ አንዴ አዲስ አበባ ሌላ ጊዜ ዋሽንግተን የሚካሄድ ሲሆን÷ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባውን በጋራ የሚመሩት ይሆናል።

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር ሦስት ምሰሶዎችን ያካተተ እንዲሆን ተስማምተዋል።

አንደኛው የኢኮኖሚ ብልጽግናን፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ሲሆን÷ በዚህ ክፍል የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ትስስር የበለጠ ማጠናከር እና ኢንቨስትመንት እና ንግድን ለማስፋት እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

ሁለተኛው የመከላከያ እና ጸጥታ ትብብርን እንደሚመለከትና በዚህም የጸጥታ ጉዳይ ትብብርን ማጠናከር እና በጋራ የደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ተሳትፎን ማጠናከርን እንደሚያካትት ተገልጿል።

የመጨረሻውን እና ሦስተኛው ምሰሶ ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋትን የተመለከተ ሲሆን÷ በዚህ ክፍል የጋራ ጥቅምን እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላምንና ደኅንነትን የሚያስጠብቁ አካሄዶችን በመፈተሽ እና በትብብር መሥራትን ያረጋግጣልም ነው የተባለው።

ይህ ቋሚ የሁለትዮሽ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ዘላቂ በሆነ መንገድ የሚያስቀጥል እና የሚያጠናክር እንደሆነ ሚኒስቴሩ አብራርቷል።

በተያያዘ መረጃ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የጸጥታ አጋርነት ለማስፋት እና የንግድ ዕድሎችን ለማሳደግ መምከራቸውን አመልክተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.