Fana: At a Speed of Life!

በሽርፍራፊ ሰከንድ የተገኘው ዋንጫ ሲታወስ…

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ሲቲ ከ44 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነበት የ2012ቱ የኢትሃድ የመጨረሻ ደቂቃ ድራማዊ ክስተት የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ሁለቱ የማንቼስተር ከተማ ክለቦች እኩል 86 ነጥቦችን በመያዝ የሊጉን ዋንጫ ለማሳካት የመጨረሻው ሳምንት ላይ የተገኙበት የ2011/12 የውድድር ዓመት እጅግ አጓጊ ነበር፡፡

በወቅቱ እስከ 32ኛ ሳምንት ድረስ ማንቼስተር ዩናይትድ የከተማ ተቀናቃኙን ማንቼስተር ሲቲ በ8 ነጥቦች ልዩነት በማስከተል ሊጉን ሲመራ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሆኖም እስከ 37ኛው ሳምንት ድረስ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 15 ነጥብ 7ቱን ብቻ ያሳካ ሲሆን፥ ማንቼስተር ሲቲ በአንጻሩ 5ቱንም በማሸነፍ በነጥብ እኩል መሆን ችሎ ነበር፡፡

በዚህም ማንቼስተር ሲቲ ነጥቡን 86 በማድረስ በ8 ግቦች በልጦ እድሉን በራሱ የሚወስንበትን የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ከኪውንስ ፓርክ ሬንጀርስ ጋር ማድረግ ጀምሯል፡፡

በተመሳሳይ 86 ነጥቦችን በመያዝ በግብ ክፍያ ተበልጦ 2ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ማንቼስተር ዩናይትድ በተመሳሳይ ሰዓት ከሰንደርላንድ ጋር ተገናኝቷል፡፡

በጣሊያናዊው አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ እየተመራ ከ44 ዓመታት በኋላ ዋንጫውን ለማሳካት ወደ ሜዳ የገባው ማንቼስተር ሲቲ እስከ 90ኛው ደቂቃ ድረስ 2 ለ 1 እየተመራ ነበር፡፡

ማንቼስተር ዩናይትድ በተመሳሳይ ሰዓት ሰንደርላንድን 1 ለ 0 ማሸነፉን ተከትሎ በስታዲየም ኦፍ ላይት የነበሩ የዩናይትድ ደጋፊዎች የውሃ ሰማያዊዎቹን ውጤት እየተመለከቱ ደስታቸውን ሲገልጹ በቴሌቪዥን መስኮት ታይተዋል፡፡

ከዚያች ቅስበት በኋላ የተፈጠረው ክስተት በዓለም የእግር ኳስ ቤተሰብ ዘንድ አይረሴ ሆኖ ዛሬም ድረስ ይታወሳል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ ከመደበኛው የጨዋታ ጊዜ መጠናቀቅ በኋላ በጭማሪ ደቂቃዎች ምናልባትም አቻ ሊወጣ ይችላል እንጂ 2 ለ 1 ከመመራት ተነስቶ ጨዋታውን ያሸንፋል ብሎ ለመገመት የሚታሰብ አልነበረም፡፡

ነገር ግን ኤዲን ዤኮ እና ኩን አጉዌሮ በ2 ደቂቃዎች ልዩነት ያስቆጠሯቸው ግቦች በእግር ኳስ የመጨረሻው ፊሽካ ካልተሰማ የሚፈጠረው አይታወቅም የሚለውን ሀሳብ በማጠናከር አይረሴውን ታሪክ መጻፍ ቻሉ፡፡

ለ44 ዓመታት ጥያቄ መልስ የተገኘባቸው እነዚያ ሽርፍራፊ ሰከንዶች በቅስበት የኢትሃድን ስታዲየም በፈንጠዚያና የደስታ እንባ ሞልተው ታይተዋል፡፡

ሊጉን ተወዳጅ ካደረጉ ሁነቶች መካከል ይህ ድራማዊ ክስተት የታየበት የ2011/12 የውድድር ዓመት የመጨረሻ ሳምንት መርሐ ግብር የተከናወነው ከ14 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬው ዕለት ነበር፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.