Fana: At a Speed of Life!

ማንቼስተር ሲቲ ወይስ ቼልሲ – ተጠባቂው የፍጻሜ ጨዋታ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ሲቲን ከቼልሲ የሚያገናኘው የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ በዌምብሌይ ስታዲየም ይደረጋል፡፡
በአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንቼስተር ሲቲ በግማሽ ፍጻሜው ሳውዛምፕተንን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ መብቃቱ ይታወሳል፡፡
ማንቼስተር ሲቲ የዘንድሮውን ጨምሮ ያለፉትን አራት ተከታታይ ዓመታት በኤፍ ኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ መገኘት ችሏል፡፡
ሆኖም ካለፉት ሦስት የኤፍ ኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ሲሆን፥ ለመጨረሻ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት የሆነው በፈረንጆቹ 2023 ነበር፡፡
ማንቼስተር ሲቲ በታሪኩ ሰባት ጊዜ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ማሳካት የቻለ ሲሆን፥ ለስምንተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡
አስቀድሞ የካራባኦ ዋንጫን ያሳካው ሲቲ በዚህ የውድድር ዓመት 2ኛ ዋንጫውን ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
በውድድር ዓመቱ የሦስትዮሽ ዋንጫ የማሳካት እድል ያለው ማንቼስተር ሲቲ ጉዞውን አጠናክሮ ለመቀጠል ይፋለማል፡፡
እስካሁን አሸናፊው ባልተለየበት የሊጉ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ማንቼስተር ሲቲ ይህንን ዋንጫ ማሳካት ከቻለ የሦስትዮሽ ዋንጫ ጉዞውን እንደሚያጠናክርለት ይታመናል፡፡
ተጋጣሚው ቼልሲ በበኩሉ በግማሽ ፍጻሜው ሊድስ ዩናይትድን በኢንዞ ፈርናንዴዝ ብቸኛ ግብ በመርታት ለፍጻሜ መድረሱ አይዘነጋም፡፡
በታሪኩ ስምንት ጊዜ የኤፍ ኤ ዋንጫን ማሳካት የቻለው የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ለ9ኛ ጊዜ በመድረኩ ሻምፒዮን ለመሆን ይፋለማል፡፡
አሰልጣኞች ቢለዋውጥም መሻሻል ያልቻለው ቼልሲ የውድድር ዓመቱን ያለምንም ዋንጫ ላለማጠናቀቅ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ለመጨረሻ ጊዜ የኤፍ ኤ ዋንጫን ማሳካት የቻለው በፈረንጆቹ 2018 እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከዚያ ወዲህ ቼልሲ በ2021 እና በ2022 የፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ቢችልም ዋንጫውን ግን ማሳካት አልቻለም፡፡
በ1871/72 በጀመረው የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ዋንጫ ውድድር አርሰናል 14 ጊዜ የዋንጫው ባለቤት በመሆን ቀዳሚው ሲሆን፥ ማንቼስተር ዩናይትድ 13 ጊዜ በመድረኩ ሻምፒዮን በመሆን ይከተላል፡፡
የዛሬ የፍጻሜ ተፋላሚው ቼልሲ፣ ሊቨርፑል እና ቶተንሃም ሆትስፐር በተመሳሳይ ስምንት ጊዜ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡
ሌላኛው የምሽቱ የፍጻሜ ተፋላሚ ማንቼስተር ሲቲ እንዲሁም አስቶንቪላ በተመሳሳይ ሰባት ጊዜ የኤፍ ኤ ዋንጫን በማንሳት በርካታ ጊዜ ሻምፒዮን ከሆኑ ቡድኖች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በዌምብሌይ ስታዲየም አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ የሚደረገውን ተጠባቂ የፍጻሜ ጨዋታ እንግሊዛዊው ዳኛ ዳረን ኢንግላንድ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.