ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቻይናን ሊጎበኙ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመጪው ሳምንት በቻይና ይፋዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ክሬምሊን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት በቻይና ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፥ በቤጂንግ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሺ ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጉብኝት በኋላ በቀናት ልዩነት የሩሲያ አቻቸውን ቭላድሚር ፑቲን ይቀበላሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ከመጪው ማክሰኞ ጀምሮ በሚያደርጉት የሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት በንግድና ኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ ከፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር እንደሚመክሩ ተገልጿል፡፡
ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የጠበቀ አጋርነትና ስትራቴጂያዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑን የፕሬዚዳንቱን ጽ/ቤት ጠቅሶ የሩሲያ የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡