Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከፈረንጆቹ 2014 በፊት ተመርተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛውን ለጤና ጎጂ የሆኑ ብናኝ ወደ ከባቢ አየር እንደሚለቁ ጥናት አመለከተ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በትራንስፖርቱ ዘርፍ የሚታየውን የብክለት መጠን ምን ያክል እንደሆነ ለማወቅ እንዲረዳ በመሳሪያ የታገዘ መረጃ በመሰብሰብ ጥናት መካሄዱን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ከሲ 40 ከተሞች የአመራሮች ቡድን ለአየር ንብረት ለውጥ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጥናቱን አካሂዷል።

በዚህም በከተማዋ ከትራንስፖርት ዘርፍ የሚለቀቀውን በካይ ጭስ በመሳሪያ የተደገፈ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት እና የአየር ጥራት ልኬት በማድረግ የከተማዋን የአየር ብክለት መጠን ያለበትን ደረጃ ለማወቅ እንደ መነሻ ጥናት እንደሚያለግል ተገልጿል፡፡

በመሆኑም ከተለያዩ የመኪና አይነቶች፣ ከሚጠቀሙት የነዳጅ አይነትና ከተመረቱበት ለምሳሌ ከፈረንጆቹ ከ1992 በፊት እና ከ2014 ወዲህ የተመረቱ ላይ ከመኪና ጭስ ማውጫ በቀጥታ ልኬት ተወስዷል።

በተወሰደው የልኬት መረጃ መሰረትም ከ2014 በፊት የተመረቱ መኪናዎች ከ72-74 ማይክሮ ግራም ፐር ሜትር ኪዩብ (µg/m3) በካይና ለጤና ጎጂ የሆኑ ብናኝ (PM2.5) ወደ ከባቢ አየር እንደሚለቁ እና እ.ኤ.አ ከ2014 ዓ.ም ወዲህ የተመረቱ መኪናዎች ደግሞ 45 ነጥብ 75 µg/m3) ማይክሮ ግራም ፐር ሜትር ኪዩብ በካይና ለጤና ጎጂ የሆኑ ብናኝ ወደ ከባቢ አየር እንደሚለቁ የመነሻ ጥናቱ ውጤት እንሚያሳይ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም ከተለያዩ የመኪና አይነቶች በተወሰደ አማቂ ጋዝ ልኬት መሰረት ከባድ መኪናዎች እስከ 45 ነጥብ 75 ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ በአመት ወደከባቢ አየር እንደሚለቁ እንዲሁም የመጓጓዣ መኪናዎች ደግሞ ከ10-30 ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ በአመት ወደ ከባቢ አየር እንደሚለቁ በንፅፅር ለማወቅ መቻሉን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የከባቢ አየር ጥራትን በተመለከተ ደግሞ ከታክሲ እና ከአውቶቢስ ፌርማታዎች ላይ በተንቀሳቃሽ የአየር ጥራት መለኪያ መሳሪያ በተወሰደ ልኬት መሰረት በካይና ለጤና ጎጂ የሆኑ ብናኝ (PM2.5) ከ26-38.5 µg/m3) የሚለቁ ሲሆን ይህም የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መለኪያ ማለትም ከ10 ማይክሮ ግራም ፐር ሜትር ኪዩብ (µg/m3 ) ጋር ሲነፃፀር ለጤና ጎጂ በሚባል ደረጃ እንዳለ እና የትራንስፖርቱን ዘርፍ በማዘመን ብክለትን የመቀነስ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባው የመነሻ ጥናቱ ውጤት አሳይቷል ተብሏል፡፡

ጥናቱ በትራንስፖርቱ ዘርፍ በሚፈጠረው ብክለት የሚያደርሰውን የጤና ጉዳት እንዲሁም በኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን ተጽእኖ በማዎቅ ወደ እርምጃ ለመግባት እና መመሪያዎችን እና ፖሊሲዎችን ለማውጣት እንደሚረዳ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ የሜይንስትሪሚንግ ቡድን መሪ ወይዘሮ ፋንቱ ክፍሌ ገልጻዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.