Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዘርባጃን የአሳን ቀላል የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትን ጎበኙ

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከዓለም የከተሞች ፎረም ተሳትፎ ጎን ለጎን የአዘርባጃን የአሳን ቀላል የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትን ጉብኝተዋል።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ እኛም እስካሁን በመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያመጣነው ከፍተኛ ለውጥ ቢሆንም አሁንም ልምድ ሊሆኑን በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

ከ14 ዓመታት በፊት የተጀመረው እና በቀን 40 ሺህ አፕሊኬሽን ላይ አገልግሎት የሚያሳልጠው አሳን÷ በአውቶቡሶች የሚሰጥ የገጠር አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የአገልግሎት ማዕከል በተደራጀ፣ ፈጣን ቀላል አገልግሎት ይሰጣሉ ነው ያሉት።

በኢትዮጵያም ከ41 በላይ ማዕከላት በመገንባት ስራ መጀመሩን ገልጸው÷ ከዚሁ ውስጥ በአዲስ አበባ 6 ማዕከላት እና 1 ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ የዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት መኖራቸውን አስታውሰዋል።

የአሳን ሰራተኞች አገልግሎት ሲሰጡ ፈገግታ እና ትህትና አንዱ የአገልግሎት መለኪያ እንደሆነ፣ የመከታተያ ካሜራዎች የተገጠሙ መሆኑን እና በጥሩ ሁኔታ የሚያገለግል ሰራተኛ ተመዝኖ እና የተገልጋዩ የዕርካታ መጠን ከፍተኛ ከሆነ ከደመወዝ በተጨማሪ ቦነስ እንደሚከፈለው ተመልክተናል ብለዋል።

በዛው ልክ በመስፈርቱ መሰረት ያላገለገለ ወዲያው ይባረራል ያሉት ከንቲባዋ÷ ለነገ ተስፋ አድገው ሕዝባቸውን በከፍተኛ ትጋትና አክብሮት የሚያገለግሉ በርካታ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች መመልከታቸውንም ገልጸዋል።

የእኛም ቢሮክራሲ በተጀመረው አግባብ ሙሉ በሙሉ እንደሚለወጥ እናምናለን፤ እንዲሳካም ተግተን እንሰራለን ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.